ልብስ በኢስላም

ልብስ በኢስላም

አንድ ሙእሚን ከሰዎች ጋር ለመደባለቅና ሠላትን ለመስገድ የሚለብሰው ልብስ፣ የሚያምርና ንጹህ መሆን አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹የአደም ልጆች ሆይ (ሃፍረተ ገላችሁን የሚሸፍኑትን) ጌጦቻችሁን በመስገጃው ሁሉ ዘንድ ያዙ፡፡›› (አል አዕራፍ 31)

አላህ (ሱ.ወ)፣ የሰው ልጅ በአለባበሱና በይፋዊ መገለጫው እንዲቆነጃጅ የሚያዘው ሕግን ደንግጓል፡፡ ይህ በራሱ የአላህን ጸጋ ይፋ ማድረግ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአላህን ጌጥ ያችን ለባሮቹ የፈጠራትን ከሲሳይም ጥሩዎቹን እርም ያደረገ ማን ነው? በላቸው እርሷ በትንሳኤ ቀን ለነዚያ ላመኑት ብቻ ስትኾን በቅርቢቱ ሕይወት ተገቢያቸው ናት፡፡ በላቸው እንደዚሁ ለሚያውቁ ሕዝቦቹ አንቀጾችን እናብራራለን፡፡›› (አል አዕራፍ 32)

 

ልብስ ብዙ ጉዳዮች ይፈጸሙበታል፡

  1. የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎችን ከእይታ ይሸፍናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የአደም ልጆች ሆይ ሃፍረተ ገላችሁን የሚሸሽግን ልብስ ጌጥንም በእርግጥ በናንተ ላይ አወረድን፡፡›› (አል አዕራፍ 26)
  2. ገላን ከሙቀትና ከውርጭ፣ እንዲሁም ከጎጂ ነገሮች ይጠብቃል፡፡ ብርድና ሙቀት ተለዋዋጭ የአየር ንብረቶች ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ)፣ የልብስን ገጽታ በማስመልከት እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሐሩርንም (ብርድንም) የሚጠብቋችሁን ልብሶች፣ የጦራችሁንም አደጋ የሚጠብቋችሁን ጥሩሮች ለናንተ አደረገላችሁ፡፡እንደዚሁ ትሰልሙ ዘንድ ጸጋውን በናንተ ላይ ይሞላል፡፡›› (አል ነሕል 81)

ኢስላም ተፈጥሯዊ ሃይማኖት ነው፡፡ በመሆኑም የሰዎችን አኗኗር አስመልክቶ የተደነገጉት ሕጎች በሙሉ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማሙና ከጤናማ አዕምሮ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡

ኢስላም ተፈጥሯዊ ሃይማኖት ነው፡፡ በመሆኑም የሰዎችን አኗኗር አስመልክቶ የተደነገጉት ሕጎች በሙሉ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማሙና ከጤናማ አዕምሮ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው፡፡

የሙስሊም አለባበስና የተፈቀዱ መቆነጃጃዎች ኢስላም የሰው ልጅን አለባበሰ የተገደበ አላደረገውም፡፡ ድንበር ማለፍ የሌለባቸው ከሆነና ለተፈለጉበት ዓላማ መዋል የሚችሉ እስከሆኑ ድረስ፣ ሁሉም የልብስ ዓይነቶች ሕጋዊ መሆናቸውን ያጸድቃል፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ በዘመኑ የነበሩ አልባሳትን ለብሰዋል፡፡ ሰዎች የተወሰኑ ልብሶች ብቻ እንዲለበሱ አላዘዙም፡፡ እንዳይለበሱ የከለከሉት ውስን ልብስም የለም፡፡ የከለከሉት በአለባበስ ዙሪያ ያሉ የተወሰኑ ገጽታዎችን ነው፡፡

በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ፣ የሁሉም ነገር መሰረቱ የተፈቀደ ነው፡፡ በማስረጃ ካልሆነ በስተቀር እርም ነው ማለት አይቻልም፡፡ ልብስ ደግሞ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ አምልኮ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ ማንኛውም ዓይነት አምልኮ መሰረቱ የተከለከለ ነው፡፡ በማስረጃ ካልሆነ በስተቀር የተፈቀደ ወይም ሕጋዊ አይሆንም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ያለማባከንና ያለኩራት ብሉ፣ መጽውቱ፣ ልበሱ፡፡›› (አል ነሳኢ 2559)

ኢስላም ልብስን በተመለከተ፣ መለበስ አለበት ብሎ የገደበው ወይም የወሰነው ልብስ የለም፡፡ በላጩና የተሻለው፣ በኢስላም የተፈቀደና የሀገሬው ነዋሪዎች የሚለብሱት የልብስ ዓይነት ነው፡፡