መተናነስ – ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል

ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል፡

 ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በስነ ምግባራቸው ከሰዎች ሁሉ የላቁ ነበሩ

 

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ እጅግ የላቀ ለሆነው የሰው ልጅ መልካም ስነ ምግባር ዓይነተኛ ተምሳሌት ነበሩ፡፡ ቁርኣን የሳቸውን ስነ ምግባር ታላቅ በማለት የገለጸው ለዚህ ነው፡፡ ባለቤታቸው እመት ዓኢሻም(ረ.ዐ) ስለርሳቸው ስነ ምግባር ሲናገሩ፡- ‹‹ስነ ምግባራቸው ቁርኣን ነበር፡፡›› ከማለት ሌላ የተሻለ የረቀቀ አገላላጽ አላገኙለትም፡፡ እርሳቸው፣ ለቁርኣን ስነ ምግባራዊ አስተምሮት ተግባራዊ ተምሳሌት ነበሩ፡፡

መተናነስ፡

  • ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እርሳቸውን በማክበርና በማላቅ አንድም ሰው እንዲቆምላቸው አይፈልጉም ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ሠሐቦቻቸውን እንዲህ ማድረግን ከልክለዋል፡፡ በመሆኑም ሠሐቦች ለርሳቸው ያላቸው ክብርና ውዴታ እጅግ ጠንካራ ከመሆኑ ጋር የእርሳቸውን መምጣት እያዩ አይቆሙላቸውም፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው፣ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር እርሳቸው እንደሚጠሉ ስላወቁ ነው፡፡ (አህመድ 12345 /አል በዛር 6637)
  • ዐዲይ ቢን ሓቲም(ረ.ዐ) ኢስላምን ሲቀበል፣ ወደርሳቸው ዘንድ መጣ፡፡ ዐዲይ፣ ከዐረብ መኳንንት አንዱ ነበር፡፡ የነብዩን(ሰ.ዐ.ወ) ጥሪ እውነታ ለማወቅ ፈለገ፡፡ ዐዲይ(ረ.ዐ) ይህንን ገጠመኝ ሲናገር፡- «እርሳቸው ዘንድ ስደርስ አንዲት ሴትና አንድ ወይም ከአንድ በላይ ሕፃናት አብረዋቸው ነበሩ፤ – ከነብዩ ጋር ያላቸውን የዝምድና ቅርበትም ጠቅሷል – በዚህን ጊዜ እነሆ እርሱ የኪስራም ሆነ የቀይሠር ንግስና ዓይነት እንዳልሆነ ተረዳሁኝ፡፡» ይላል፡፡ (አህመድ 19381) መተናነስ የነብያት ሁሉ መገለጫ ባህሪ ነው፡፡
  • ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከባልደረቦቻቸው ጋር ሲቀመጡ፣ ከነርሱ መካከል እንደሆነ አንድ ተራ ሰው ነበር፡፡ ከነሱ የሚለዩበት ምንም ነገር አይታይባቸውም፡፡ በዙሪያቸው ከሚቀመጡት የሚለያቸው የሆነ ስፍራም አይቀመጡም፡፡ የማያቃቸው እንግዳ ሰው በተቀመጡበት ቦታ በድንገት በሚገባ ጊዜ፣ እርሳቸውን ከባልደረቦቻቸው ለይቶ ማወቅ አይችልም፡፡ እናም «ከመካከላችሁ ሙሐመድ የትኛችሁ ነው? « በማለት ይጠይቅ ነበር፡፡ (አል ቡኻሪ 63)
  • አነስ ቢን ማሊክ እንዲህ ብለዋል፡- «ከመዲና ባሮች መካከል የሆነች አንዲት ባሪያ፣ ጉዳይዋን እንዲያስፈፅሙላት የነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) እጅ ይዛ የፈለገችበት ቦታ ትሄድ ነበር፡፡» (አል ቡኻሪ 5724) ‹‹እጃቸውን ይዛ›› የሚለው ሐረግ፣ ለትንሹም ለደካማውም የነበራቸውን እሺታና ገራገርነት ለመግለፅ የተጠቀሙበት ነው፡፡ ይህ፣ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመተናነስ ላይ የነበራቸውን ባህሪ ድካ በደረሰ መልኩ ይገልፃል፡፡ ምክንያቱም በታሪኩ ላይ የተጠቀሰው ወንድ ሳይሆን ሴት፤ ነፃ ሳትሆን ባሪያ ነች፡፡ ከመሆኑም ጋር ጉዳይዋን እንዲያስፈፅሙላት የፈለገችበት ስፍራ ይዛቸው ትሄድ ነበር፡፡
  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በልቡ ውስጥ የቅንጣት ክብደት ያህል ኩራት ያለበት ሰው ጀነት አይገባም፡፡›› (ሙስሊም 91)