ምጽዋት ሊወጣለት ግዴታ የሚሆን ንብረት የትኛው ነው?

ምጽዋት ሊወጣለት ግዴታ የሚሆን ንብረት የትኛው ነው?

አንድ ሰው ለራሱ በሚጠቀምበት ንብረቱ ላይ ምጽዋት የማውጣት ግዳጅ የለበትም፡፡ ለምሳሌ፣ ዋጋው ምንም ያህል ቢወደድም የሚኖሪያ ቤቱ፣ እንዴትም ያለ ዘመናዊና የቅንጦት ቢሆንም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበት መኪናው ላይ፣ ምጽዋት የማውጣት ግዴታ የለበትም፡፡ በሚለብሰው፣ በሚበላውና በሚጠጣውም ነገር ላይ እንዲሁ የግዴታ ምጽዋት የለበትም፡፡

አላህ (ሱ.ወ) ምጽዋትን ግዴታ ያደረገው በግል ጉዳይ ላይ ግልጋሎት የማይሰጡ በሆኑ የተለያዩ ንብረቶች ላይ ሲሆን እነኚህ ንብረቶች በባሕሪያቸው እየጨመሩና እየፋፉ የሚሄዱ ናቸው፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. ለጌጥነትና ለውበት የማይለበስ የሆነ ወርቅና ብር

የወርቅና የብር ክምችትም ሆነ ማንኛውም ንብረት፣ ኢስላማዊው ሕግ የገደበውን መጠን (ሂሣብ) ካልሞላ፣ እንዲሁም ሳይቀንስ አንድ የጨረቃ ዓመት ማለትም 354 ቀናቶች ካልዞረበት በስተቀር ምጽዋት(ዘካ) ሊወጣበት ግዳጅ አይሆንም፡፡

በሁለቱ ማዕድናት ምጽዋት የማውጪያ መጠን (ሂሣብ)

ሂሣብ፣ ለወርቅ 85 ግራምና ከዚያ በላይ ለብር ደግሞ 595 ግራምና ከዚያ በላይ ነው፡፡

አንድ ሙስሊም ይህን መጠን የሚደርስ ወርቅ ወይም ብር ካለውና አንድ ዓመት ከዞረበት፣ ከንብረቱ 2.5 ፐርሰንቱን ይመጸውታል(ዘካ ያወጣል)፡፡

  1. ተቀማጭ ገንዘብና የተለያዩ የመገበያያ ኖቶች እንደ ዓይነታቸው በካሽ በእጁ ያለ ወይም በባንክ አካውንት ውስጥ የሚገኝ ገንዘብ ዘካ ይወጣለታል፡፡

የግዴታ ምጽዋት(ዘካ) አወጣጥ፡ የገንዘቡንና የመገበያያውን ነገር ሊገዛ ከሚችለው የወርቅ መጠን ጋር በማስላት፣ መጠኑ ወርቅ ዘካ ከሚወጣበት ሂሣብ ጋር እኩል ከሆነና ከዚያም ከበለጠ ዘካ ያወጣለታል፡፡ ገንዘቡ ከ85 ግራም ወርቅ ጋር ከተስተካከለ ወይም ከበለጠ፣ እንዲሁም በሰውዬው ይዞታ ስር ኾኖ ሳይቀንስ አንድ የጨረቃ ዓመት ካለፈበት፣ የንብረቱን 2.5 ፐርሰንት ዘካ ያወጣል፡፡

የወርቅ ዋጋ ከፍ፣ ዝቅ ሊል፣ ሊወዋወጥ ይችላል፡፡ በአንድ ሰው ላይ ዘካ ማውጣት ግዳጅ በሚሆንበት ወቅት የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ 25 ዶላር ነው ብለን ብናስብ፣ በዚያ ወቅት የዘካ ማውጫ መጠን ወይም ሂሣብ የሚከተለው ይሆናል፡፡

25 ዶላር/ግ.ም X 85ግ.ም = 2125 ዶላር ይሆናል፡፡ 85ግ.ም- ምጽዋት ማውጣት ግዳጅ የሚሆንበት የወርቅ መጠን ሲሆን ይህ ቋሚና የማይለወጥ ነው፡፡ 2125 ዶላር-በቀረበው ምሳሌ መሰረት ዘካ ግዳጅ የሚሆንበት የገንዘብ መጠን(ሂሣብ) ነው፡፡ ስለዚህ የዘካው መጠን- 2.5% X 2125 ዶላር = 53.125 ዶላር ይሆናል፡፡

  1. ለንግድ የቀረቡ ዕቃዎች

ለንግድ የተዘጋጁ፣ እንደ ሪል ኢስቴቶች፣ ቤቶች፣ ሕንፃዎች ያሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፡ ወይንም ምግብ ነክ አና አላቂ ሸቀጦች በዚህ ስር ይገባሉ፡፡

የዘካው አወጠጥ፡ ነጋዴው ለንግድ ዕቃዎቹን በሙሉ ዓመት ዞሮባቸው ከሆነ ዋጋቸውን ያሰላል፡፡ የሚያሰላበት ዋጋም ዘካውን ሊያወጣ በተነሳበት ዕለት ባለው የገበያ ዋጋ መሰረት ነው፡፡ የቃዎቹ ዋጋ የዘካ ማውጫ መጠን (ሂሣብ) ከደረሰ፣ ከሱ ላይ 2.5 ፐርሰንት ዘካ ያወጣለታል፡፡

 

  1. ከምድር የሚበቅሉ፡ አዝመራ፣ ፍራፎዎችና የእህል አይነቶች

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ ካፈራችሁትና ከዚያም ለናንተ ከምድር ካወጣንላችሁ ከመልካሙ ለግሱ፡፡›› (አል በቀራ 267)

ዘካ ማውጣት ግዴታ የሚሆነው በተወሰኑ የአዝርዕት ዓይነቶች ላይ እንጂ በሁሉም አይደለም፡፡ ይህም በኢስላማዊው ድንጋጌ መሰረት ዘካ የሚወጣለትን መጠን ከደረሰ ብቻ ነው፡፡

የሰዎችን ልፋትና ድካም ከግምት ውስጥ ከማስገባት አንጻር፣ ዘካ የሚወጣው ብዛት በዝናብና በወንዝ ውሃ በለሙና በሰው ኃይል ወይም መስኖ በለሙት መካከል ልዩነት አለው፡፡

  1. እንደ ላም፣ ግመልና ፍየል ያሉ የእንሰሳት ሃብት፡ ባለሃብቱ፣ እነሱን በመቀለብ የማይቸገርና የማይለፋ ከሆነ እንዲሁም በግጦሽ ላይ ተሰማርተው ውለው የሚገቡ ከሆነ ዘካ ይወጣላቸዋል፡፡

የሚወጣበትን መጠን (ኒሣብ) የሚወጣለትን መጠንና የመሳሰሉትን ዝርዝር መረጃዎች ከፊቂህ መጽሐፍት ላይ የምናገኘው ይሆናል፡፡