ሠላተል ጀማዓ (በሕብረት መስገድ)

ሠላተል ጀማዓ (በሕብረት መስገድ)

አላህ(ሱ.ወ) ወንዶችን በሕብረት እንዲሰግዱ አዟቸዋል፡፡ ሠላተል ጀማዓ ትልቅ ምንዳ እንዳለውና ልቅናውን የሚናገሩ ሐዲሶች ወርደዋል፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹የሕብረት ሠላት ከነጠላ ሠላት በሃያ ሰባት ደረጃ ይበልጣል፡፡›› ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 619 / ሙስሊም 650)

የሠላተል ጀማዓ ትንሹ ቁጥር ኢማምና አንድ ተከታይ ነው፡፡ የጀመዓው ቁጥር በበዛው ልክ አላህ ዘንድ ያለውም ተወዳጅነት ይጨምራል፡፡

የመከተል ትርጉም፡

መከተል ማለት፣ አንድ ተከትሎ የሚሰግድ ሰው ሠላቱን በኢማሙ ማሰሩ ነው፡፡ ተከትሎ የሚሰግደው ሰው ኢማሙን በሩኩዑ፣ በሱጁዱ ይከተለዋል፡፡ የቁርኣን ንባቡን ደግሞ ያዳምጠዋል፡፡ ኢማሙን ሊቀድመው ወይም ከርሱ ወደ ኋላ መቅረት አይገባውም፤ ይልቁንም ኢማሙ የሚሰራውን ነገር በቶሎ እየተከተለ ይተገብራል፡፡

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ እነሆ ኢማም የተደረገው ሊከተሉት ነው፡፡ አላሁ አክበር ሲል አላሁ አክበር በሉ፤ አላሁ አክበር እስኪልም ቀድማችሁ አላሁ አክበር አትበሉ፤ ሲያጎነብስ አጎንብሱ፣ እስኪያጎነብስ ድረስም አታጎንብሱ፤ ሰሚዐላሁ ሊመን ሐሚደሁ ሲል፣ ረበና ወለከል ሐምዱ በሉ፤ ሲሰግድም ስገዱ፤ እስኪሰግድ ድረስም አትስገዱ…..›› (አል ቡኻሪ 701/ ሙስሊም 414 / አቡዳውድ 603)

ለኢማምነት የሚቀደመው ማን ነው?

የአላህን መጽሐፍ በቃሉ የሸመደደ ሰው ለኢማምነት ይቀደማል፡፡ ከርሱ በመለስ ያለው ይከተለዋል እንዲህም እያለ ይቀጥላል፡፡ ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የአላህን መጽሐፍ ይበልጥ አሳምሮ የሚያነብ ሰው ለኢማምነት ይቀደማል፡፡ በንባብም የሚስተካከሉ ከሆነ ደግሞ ይበልጥ ፈለጌን(ሱናን) የሚያውቀው ይቀደማል፡፡….›› (ሙስሊም 673)

ኢማሙና ተከታዮቹ የሙቆሙት የት ነው?

ኢማሙ ከፊታቸው መሆን አለበት፡፡ ተከታዮቹ ደግሞ፣ የመጀመሪያውን ሠፍ ብሎ የሚቀጥለውን እያሟሉ ተስተካክለው መቆም አለባቸው፡፡ ተከታዩ አንድ ከሆነ ደግሞ ከኢማሙ በስተቀኝ በኩል ይቆማል፡፡

ኢማም ተከትሎ ሲሰግድ ያመለጠውን ሠላት እንዴት ይሞላዋል?

ከሠላት የተወሰነ ክፍል አምልጦት ኢማሙን የተከተለ ሰው፣ ኢማሙ ኢስኪያሰናብት ተከትሎ ይሰግድና ከዚያም ቀሪዉን ይሞላል፡፡

ከኢማሙ ጋር ያገኘውን የሠላት ክፍል እንደ ሠላቱ መጀመሪያ፣ቀጥሎ የሚሰራውን ደግሞ እንደ ሠላቱ መጨረሻ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡

ረከዓ በምን ትገኛለች?

ሠላትን የምንቆጥረው በረከዓዎች ቁጥር ነው፡፡ ከኢማሙ ጋር ሩኩዕ ላይ የደረሰ ሰው ሙሉ ረከዓን አግኝቷል፡፡ ሩኩዕ ያመለጠው ሰው ደግሞ ኢማሙን ተከትሎ ወደ ሠላት ይገባል ነግር ግን ከዚያች ረከዓ ያመለጠው ስራና ንግግር ከረከዓዎቹ አይቆጠሩም፡፡

ከኢማሙ የመጀመሪያው የሠላት ክፍል ያመለጠው ሰው ምሳሌ፡

ከፈጅር ሠላት፣ ከኢማሙ ጋር ሁለተኛዋን ረከዓ ያገኘ ሰው፣ ኢማሙ ካሰላመተ በኋላ ቆሞ ያለፈችውን አንድ ረከዓ ማሟላት አለበት፡፡ አጠናቆ እስኪሰግድ ድረስ ማሰላመት የለበትም፤ ምክንያቱም የፈጅር ሠላት ረከዓ ቁጥር ሁለት ነው፤ እርሱ ደግሞ ያገኘው አንዷን በመሆኑ የተቀረውን ማሟላት አለበት፡፡

የዙሁር ሠላት ላይ፣ በሦስተኛዋ ረከዓ፣ ኢማሙን ሩኩዕ ላይ ያገኘው ሰው፣ ከኢማሙ ጋር ሁለት ረከዓዎችን አግኝቷል፡፡ ይህ ማለት ለተከትሎ ሰጋጁ ከዙሁር ሠላት የመጀመሪያዎቹን ሁለት ረከዓዎች ሰገደ ማለት ነው፡፡ ኢማሙ ካሰናበተ በኋላ ቆሞ የተቀረውን ማሟላት አለበት፡፡ ዙሁር ባለ አራት ረከዓ ስለሆነ፣ ቆሞ የሚሞላቸው ረከዓዎች ሦስተኛዋንና አራተኛዋን ይሆናል ማለት ነው፡፡

ኢማሙ ከመግሪብ ሠላት በመጨረሻው ተሸሁድ ላይ ሆኖ ያገኘው ሰው፣ ኢማሙ ካሰላመተ በኋላ ሦስት ሙሉ ረከዓዎችን መስገድ አለበት፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ እርሱ ኢማሙን ያገኘው በመጨረሻው ተሸሁድ ላይ ነው፤ ረከዓን ማግኘት የሚቻለው ግን ከኢማሙ ጋር ሩኩዕ ላይ በመድረስ ስለሆነ ነው፡፡