ሱጁደ ሰህው

ሱጁደ ሰህው

ሱጁደ ሰህው፣ ሁለት ሱጁዶችን ማድረግ ሲሆን በሠላት ውስጥ ለሚከሰቱ ጉድለቶችና ክፍተቶች ማካካሻና መጠገኛነት የተደነገገ ነው፡፡

ሱጁደ ሰህው ማድረግ የሚፈቀደው መቼ ነው?

በሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ሱጁደ ሰህው ይደረጋል፡

  1. አንድ ሰጋጅ በመርሳትና በስህተት ምክንያት በሠላቱ ውስጥ ተጨማሪ ሩኩዕን ወይም ሱጁዱን ወይም መቆም ወይም መቀመጥን ከጨመረ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡
  2. ከሠላት ማዕዘናት መካከል አንዱን ማዕዘን ካጎደላ፣ ያንን ያጎደለውን ማዕዘን ያሟላና በሠላቱ ማብቂያ ላይ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡
  3. እንደ ተሸሁደል አወል(የመጀመሪያው መቀመጥ) ዓይነት ከሠላት ግዴታዎች መካከል አንዱን ረስቶ ከተወ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡
  4. የሰገዳቸውን የረከዓት ቁጥር ከተጠራጠረ፣ መጀመሪያ እርግጠኛ የሆነውን፣አነስተኛውን ቁጥር ይይዝና ካሟላ በኋላ ሰጅደተ ሰህው ይሰግዳል፡፡

የአሰጋገዱ ዓይነት፡ በመደበኛ ሠላቱ ውስጥ እንዳለው ሱጁድና መቀመጥ ዓይነት፣ በሱጁዶቹ መሐከል የሚቀመጥ ሆኖ ሁለት ሱጁዶችን ይሰግዳል፡፡

ሱጁድ የማድረጊያው ጊዜ፡ ሱጁደ ሰህው ሁለት ጊዜዎች አሉት፤ ሰጋጁ ከሁለቱ በአንዱ በፈለግው ጊዜ ሊሰግደው ይችላል፡፡

  • ከመጨረሻው ተሸሁድ በኋላ ይሰግዳትና ከዚያም ያሰላምታል፡፡
  • ሠላቱን በሰላምታ ካሰናበተ በኋላ ሁለት ሱጁዶችን ስግዶ፣ ለሁለተኛ ጊዜ በሰላምታ ያሰናብታል፡፡