ሴት በኢስላም ውስጥ ያላት ስፍራ

ሴት በኢስላም ውስጥ ያላት ስፍራ

ኢስላም ሴት ልጅን እጅግ በጣም አክብሯታል፡፡ ለወንዶች ባሪያ ከመሆንም ነፃ አውጥቷል፡፡ ክብርና ደረጃ የሌላት ውዳቂና ርካሽ ከመሆንም አድኗታል፡፡ ከሴት ልጅ ክብር ጋር ተያያዥነት ካላቸው ኢስላማዊ ድንጋጌዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  • ኢስላም ለሴት ልጅ ፍትሃዊ በሆነ ክፍፍሎሽ የውርስ ድርሻዋን ሰጥቷል፡፡ በአንዳንድ ስፍራ ከወንድ ጋር እኩል ታገኛለች፡፡ በአንዳንድ ስፍራ ደግሞ ድርሻዋ ከወንዱ ይለያል፡፡ ይኸውም ለሟች ባላት ቅርበት፣ እንዲሁም ካለባት ኃላፊነትና ወጪ አንጻር የሚወሰን ነው፡፡
  • በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ወንድና ሴትን እኩል አድርጓቸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ማንኛውም ገንዘብ ነክ እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሴቶች የወንዶች ክፋይ ናቸው፡፡›› (አቡ ዳውድ 236)
  • ኢስላም ለሴት ልጅ ባሏን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል፡፡ ልጆችን የማሳደግ ትልቅ ኃላፊነት ደግሞ ጥሎባታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሴት ልጅ በባሏ ቤት ውስጥ ጠባቂ ነች፤ ከምትጠብቀው ነገር ተጠያቂ ነች፡፡›› (አል ቡኻሪ 853 / ሙስሊም 1829)
  • ስሟና በአባት የመጠራት ክብሯ እንዲቆይ አድርጎላታል፡፡ ከጋብቻ በኋላም በአባት መጠራቷ ይቀጥላል፡፡ ምን ጊዜም በአባቷና በቤተሰቦቿ መጠራቷም ይዘልቃል፡፡
  • ወጪያቸውን መሸፈን ከሚኖርበት ሴቶች መካከል ከሆነች ማለትም ሚስቱ እናቱ ወይም ሴት ልጁ ከሆነች፣ ኢስላም በወንዱ ላይ እሷን የመጠበቅና ወጪዋን የመሸፈን ግዴታ ጥሎበታል፡፡
  • የቅርብ ዘመድ ባትሆንም፣ ረዳት የሌላትን ደካማ ሴት መርዳትና ማገዝ ልዩ ክብርና ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡ እሷን ለመርዳትና ለማገዝ መሯሯጥ አላህ ዘንድ ትልቅ ክብር ያለው ተግባር መሆኑን በመግለጽ አነሳስቷል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና የችግረኞችን ጉዳይ ለመፈፀም የሚሯሯጥ ሰው፣ ልክ በአላህ መንገድ ላይ ትግል እንደሚያደርግ፣ ሌሊት ተነስቶ ሳይታክት እንደሚሰግድና፤ ጾሞ እንደማያፈጥር ሰው ነው፡፡›› (አልቡኻሪ 5661 / ሙስሊም 2982)

ኢስላም ልዩ ትኩረት እንዲቸራቸው ያደረጋቸው ሴቶች

እናት፡ አቡ ሁረይራ(ረ.ዐ) የሚከተለውን ሐዲስ አስተላልፈዋል፡፡ አንድ ሰው ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣና፣ አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ ከሰዎች ሁሉ በበለጠ ጓደኝነቱን ወይም ግንኙነቱን ልጠብቅለት የሚገባ ማን ነው? አላቸው፡፡ እሳቸውም፡ ‹‹እናትህ›› አሉት፤ ከዚያስ? አላቸው፤ ‹‹ከዚያም እናትህ›› አሉት፤ ከዚያስ? አላቸው፤ ‹‹አሁንም እናትህ›› አሉት፡፡ ለአራተኛ ጊዜ፡ ከዚያስ? አላቸው፣ ‹‹ከዚያማ አባትህ ነው፡፡›› አሉት፡፡ (አል ቡኻሪ 5626 / ሙስሊም 2548)

ሴት ልጅ፡ ዑቅበቱ ኢብኑ ዓሚር(ረ.ዐ) ነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ብለዋል፡ ‹‹ሦስት ሴት ልጆች ኖረውት፤ ስለነርሱ ትዕግስት አድርጎ፣ ጥሮ ግሮ ከላቡ ውጤት ያበላቸው፣ ያጠጣቸውና፣ ያለበሳቸው ሰው፣ የትንሳኤ ቀን ከእሳት ግርዶሽ ይሆኑለታል፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 3669)

ሚስት፡ እመት ዓኢሻ(ረ.ዐ)፣ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸውን አስተላልፈዋል፡- ‹‹በላጫችሁ ለቤተሰቦቹ መልካም የሆነው ነው፡፡ እኔ ለቤተሰቦቼ መልካማችሁ ነኝ፡፡›› (አል ቲርሚዚ 3895)