ስነ-ምግባር በኢስላም ውስጥ ያለው ስፍራ

ስነ-ምግባር በኢስላም ውስጥ ያለው ስፍራ

  1. ስነ-ምግባር፣ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ሰው ዘር ከተላኩበት ዓላማዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡

አላህ (ሱ.ወ) ነቢዩን (ሰ.ዐ.ወ) አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱ ያ በመሃይሞቹ ውስጥ አንቀጾቹን (ቁርአንን) በነርሱ ላይ የሚያነብላቸው፣ (ከማጋራት) የሚያጠራቸውም… የኾነን መልክተኛ የላከ ነው፡፡›› (ጁምዓ 2 ) በአአንቀጹ ላይ፣ አላህ (ሱ.ወ) ለምእመናን ቁርኣንን እንዲያስተምራቸውና ከእኩይ ስነ-ምግባር እንዲያጠራቸው መልክተኛውን በመላኩ የዋለውን ውለታ አውስቷል፡፡ እራስን ማጥራት ወይም ተዝኪያ፡- ቀልብን በአላህ ከማጋራት እንዲሁም እንደ ቂምና ምቀኝነት ካሉ እኩይ ስነ-ምግባሮች፣ ንግግርና ተግባርን ደግሞ ከተወገዙ ልማዶች ማጥራትን ያካትታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አሻሚ ባልሆነ ግልጽ ቃላቸው እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እነሆ እኔ የተላኩት መልካም ስነ-ምግባሮችን ላሟላ ዘንድ ነው፡፡›› (አል በይሃቂ 21301) ለነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) መላክ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ግላዊና ማህበራዊ ስነ-ምግባሮችን ማሳደግና ማረቅ ነው፡፡

  1. ስነ-ምግባር ዋነኛ የእምነት ክፍል ነው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በኢማኑ በላጩ አማኝ የትኛው ነው? ተብሎ በተጠየቁ ጊዜ፡ ‹‹በስነምግባሩ በላጫችሁ ነው ብለዋል፡፡›› (አል ቲርሚዚ 1162 /አቡ ዳውድ 4682)

 ስነ ምግባርን ማሟላት ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የተልዕኮ ዓላማዎች ዋነኛው ነው

አላህ (ሱ.ወ) ኢማንን በጎ ነገር በሚል አውስቶታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹መልካም ስራ፣ ፊቶቻችሁን ወደ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ ማዞር አይደለም፤ ግን መልካም ስራ በአላህና በመጨረሻው ቀን፣ በመላእክትም፣ በመጻሕፍትም፣ በነብያትም ያመነ ሰው….(ስራ) ነው፡፡›› (አል በቀራ 177) መልካም ነገር (ቢር)፡ በጎ ነገሮችን ከስነ-ምግባር፣ ከንግግርና ከተግባር ጋር የሚያቆራኝ ጥቅላዊ ስያሜ ወይም መጠሪያ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹መልካም ነገር ጥሩ ስነ ምግባር ነው፡፡›› ያሉት ለዚህ ነው፡፡ (ሙስሊም 2553) ይህ ጉዳይ በይበልጥ ግልጽ የሚሆነው በሚከተለው የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር ውስጥ ነው፡- ‹‹ኢማን ከስልሳ ሦስት እስከ ስልሳ ዘጠኝ ደረጃዎች አሉት፤ ከፍተኛው ላኢላሃኢለላህ የሚለው ቃል ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ ከመንገድ ላይ ቆሻሻን ማስወገድ ነው፤ ህፍረትም ከኢማን ክፍል ነው፡፡›› (ሙስሊም 35)

  1. ስነ-ምግባር ከእያንዳንዱ የአምልኮ ዘርፍ ጋር የተሳሰረና የተቆራኘ ነው አላህ (ሱ.ወ) አንድንም የአምልኮ ዓይነት ሲያዝ ስነምግባራዊ ዓላማውን ወይም በግለሰብና በማህበረሰብ ላይ የሚያስገኘውን ለውጥ ወይንም የሚጥለውን ፋና አብሮ ያሳስባል ወይም ይገልጻል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ፤ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ሠላት፡ ‹‹ሠላትንም (ደንቡን ጠብቀህ) ስገድ፤ ሠላት ከመጥፎና ከሚጠላ ነገር ሁሉ ትከለክላለችና፡፡›› (አል አንከቡት 45) ዘካ፡ ‹‹ከገንዘቦቻቸው ስትኾን በርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ፡፡›› (አል ተውባ 103) በመሰረቱ፣ ዘካ ለሰዎች በጎ መዋል፣ እነርሱን መደገፍና መርዳት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ፣ የሰጪውን ክፍል ነፍስ ከመጥፎ ስነ-ምግባሮች ያጠራለታል፡፡ ጾም፡ ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡›› (አል በቀራ183) የጾም ዓላማው፣ ትዕዛዙን በመፈፀምና የተከለከለውን በመራቅ አላህን መፍራት ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹የውሸት ንግግርና በርሱ መስራትን ያልተወ ሰው፣ ምግብና መጠጡን ከመተው አላህ ጉዳይ የለውም፡፡›› ብለው የተናገሩት ለዚህ ነው፡፡ (አል ቡኻሪ 1804) መጾሙ ከሰዎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት ስነ-ምግባራዊ ለውጥ ያላመጣለት ሰው በርሱ ላይ የጾም ዓላማ አልተረጋገጠበትም፡፡

  1. አላህ (ሱ.ወ) ለጥሩ ስነ-ምግባር ያዘጋጀው የላቀ ደረጃና ከባድ ምንዳ በዚህ ዙሪያ በርካታ የቁርኣንና የሐዲስ ማስረጃዎች ተላልፈዋል፡፡ ከነሱም መካከል፡
  • በትንሳኤ ቀን በሚዛን ላይ እጅግ በጣም ክብደት ከሚያነሱ ወይም ከሚደፉ መልካም ስራዎች መካከል ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በሚዛን ላይ ተደርጎ ከጥሩ ስነ- ምግባር የበለጠ የሚከብድ ነገር የለም፤ የጥሩ ስነ-ምግባር ባለቤት የጾመኛና የሰጋጅ ደረጃን በርሱ ይደርሳል፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2003)
  • ጀነት ለመግባት ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹የሰው ልጅን በብዛት ጀነት የሚያስገባው፣ አላህን መፍራትና ሰናይ ስነ-ምግባር ነው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2004 /ኢብኒ ማጃህ 4246)
  • የጥሩ ስነ ምግባር ባለቤት የትንሳኤ ቀን ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እጅግ የቀረበ ይሆናል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በትንሳኤው ቀን እኔ ዘንድ እጅግ ተወዳጃችሁና በስፍራም ለኔ የበለጠ ቅርባችሁ፣ ከናንተ መካከል በስነ ምግባሩ በላጫችሁ ነው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2018)
  • በጀነት ከፍተኛውን ማዕረግ እንደሚያገኝ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዋስትና ሰጥተውታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እውነቱ እርሱ ዘንድ ቢሆንም ሙግትን ለተወ ሰው፣ በጀነት ዳርቻ የሆነ ቤትን፣ ለቀልድ ቢሆንም ውሸትን ለተወ ሰው ደግሞ በጀነት መሐል የሆነ ቤትን፤ ስነ-ምግባሩ ላማረ ሰው ደግሞ በጀነት የላይኛው ክፍል የሚገኝ ቤትን ዋስትና እሰጠዋለሁ፡፡›› (አቡ ዳውድ 4800)