በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነብይነትና መልዕክተኝነት ማመን

በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነብይነትና መልዕክተኝነት ማመን

 • ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የአላህ ባሪያና መልዕክተኛ መሆናቸውን እናምናለን፡፡ እርሳቸው የመጀመሪያዎችም የኋለኞችም አለቃና የነብያት መቋጫ ናቸው፡፡ ከርሳቸው ብኋላ የሚነሳ ነብይ የለም፡፡ መልዕክታቸውን አድርሰዋል፡፡ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡ ሕዝባቸውን መክረዋል፡፡ በአላህ መንገድ መታገል የሚገባቸውን ያክል ታግለዋል፡፡
 • እርሳቸው የተናገሩትን በሙሉ እንቀበላለን፡፡ ያዘዙትን እንተገብራለን፡፡ ከከለከሉትና ካስጠነቀቁት ነገር እንርቃለን፡፡ እርሳቸው በዘረጉልን መስመር መሰረት አላህን እንገዛለን፡፡ ከርሳቸው ባሻገር ማንንም በአርዓያነት አንከተልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ለናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለኾነ ሰው አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልዕክተኛ መልካም መከተል አላችሁ፡፡» (አል አሕዛብ 21)
 • ለወላጅ፣ ለልጅ፣ በአጠቃላይ ለሰዎች ካለን ውዴታ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ውዴታ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- «አንዳችሁም እኔ እርሱ ዘንድ ከወላጆቹ፣ ከልጆቹና ከሰዎች በሙሉ የበለጠ ተወዳጅ እስካልሆንኩ ድረስ አያምንም፡፡» (አል ቡኻሪ 15/ ሙስሊም 44) እርሳቸውን በትክክል መውደድ ማለት ፈለጋቸውን መከተል፣ መመሪያቸውን መንገድ ማድረግ ነው፡፡ ትክክለኛ ደስታም ሆነ ሙሉዕ መመራት ሊረጋገጥ የሚችለው እርሳቸውን በመታዘዝ ብቻ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ብትታዘዙትም ትመራላችሁ፤ በመልክተኛውም ላይ ግልጽ ማድረስ እንጂ ሌላ የለበትም፡፡» (አል ኑር 54)
 • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተላለፉትን በሙሉ መቀበል አለብን፡፡ ለፈለጋቸውም ታዛዦች መሆን ይኖርብናል፡፡ የእርሳቸውን መመሪያ ትልቅ ስፍራና ክብር ልንቸረው ያስፈልጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ፣ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍፁም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፡፡» (አል ኒሳእ 65)
 • የእርሳቸውን ትዕዛዝ ከመጻረርና ከመቃረን ልንጠቀቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የርሳቸውን ትዕዛዝ መቃረን ለፈተና፣ ለጥመትና ለአሳማሚ ቅጣት ይዳርጋል፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ» (አል ኑር 63)

የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት ልዩ ይዘት

የነብዩ ሙሐመድ መልክት ከቀደምት መልዕክቶች ለየት የሚያደርጉት በርካታ ይዘቶች አሉት፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

 • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት የቀደምት መልዕክቶችን መልዕክት የሚቋጭ መሆኑ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ሙሐመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም፡፡ ግን የአላህ መልዕክተኛና የነብዮች መደምደሚያ ነው፡፡» (አል አሕዛብ 40)
 • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልዕክት ቀደምት መልዕክቶችን የተካ መሆኑ፡፡ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ከተላኩ ብኋላ አላህ (ሱ.ወ) እርሳቸውን ከመከተል ውጭ ምንም ዓይነት ሃይማኖትን አይቀበልም፡፡ በርሳቸው ጎዳና እንጂ አንድም ሰው ወደ ጀነት ጸጋ መድረስ አይችልም፡፡ እርሳቸው ከመልዕክተኞች ሁሉ የተከበሩ ናቸው፡፡ ሕዝባቸውም ከሕዝቦች ሁሉ ምርጥና በላጭ ሕዝብ ነው፡፡ ሕግጋታቸውም ከሕግጋት ሁሉ የተሻለና የተሟላ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰው ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለውም እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎቹ ነው፡፡» (አል ዒምራን 85)

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፡ ከዚህ ሕዝብ ውስጥ የሁድም ሆነ ክርስቲያን አንድም ሰው ስለኔ ሰምቶ በተላኩበት የማያምን አይኖርም ከእሳት ጓዶች ቢሆን እንጂ» (ሙስሊም 153 / አህመድ 8609)

 • የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መልክት ሁለቱንም ፍጡሮች ማለትም አጋንንትንም ሰውንም የሚመለከት መሆኑ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ጅኖች ያሉትን ሲያወሳ እንዲህ ብሏል፡- «ወገኖቻችን ሆይ የአላህን ጠሪ ተቀበሉ፡፡»

((አል አሕቃፍ 31) « አንተንም ለሰዎች ሁሉ በመላ አብሳሪና አስፈራሪ አድርገን ቢኾን እንጂ አልላክንህም ፡፡» (ሰበእ 28) ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡ «በስድስት ነገሮች ከነብያት ተልቄያለሁ፡ ጥቅላዊ የንግገር ስልትን ተሰጥቻለሁ፤ ጠላትን በማስፈራት ታግዣለሁ፣ ምርኮ ተፈቅዶልኛል፣ ምድር ንፁሕና የጸሎት ስፍራ ተደርጋልኛለች፣ ወደ ፍጡራን በመሉ ተልኬያለሁ፣ ነብያት በእኔ ተደምድመዋል፡፡» (አል ቡኻሪ 2815 / ሙስሊም 523)

በመልዕክተኞች የማመን ጥቅም ወይም ፍሬ

በመልዕክተኞች ማመን ከባድ ጥቅም አለው ከነዚህም መካከል

 1. አላህ(ሱ.ወ0 ለባሮቹ ያለውን ርህራሄና እንክብካቤ ማወቅ፡ ይኸውም መልዕክተኞቹን ወደ ነርሱ በመላክ ወደ ቀጥተኛው ጎዳና እንዲመሯቸውና በምን መልኩ አላህን ማምለክ እንዳለባቸው እንዲያብራሩላቸው በማድረጉ ነው፡፡ የሰው ልጅ አዕምሮ ይህን የማወቅ ችሎታ የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ስለ ነብያችን ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡- «(ሙሐመድ ሆይ) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም፡፡» (አል አንቢያእ 117)

 2. በዚህ ታላቅ ጸጋው ላይ አላህን ማመስገን

 3. መልዕክተኞችን መውደድ፣ ማላቅና ለነሱ በሚገባ መልኩ እነሱን ማድነቅና ማሞገስ፡፡ ምክንያቱም እነሱ አላህን በመገዛት፣ መልዕክቱን በማድረስና ለባሮቹ መልካምን በማስተማር ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋልና ነው፡፡

 4. መልዕክተኞች ከአላህ ዘንድ የተላኩበትንና ይዘው የመጡትን መልዕክት መከተል፡ እሱም አላህን በብቸኝነት ማምለክና ለርሱ ተጋሪ አለማድረግ ነው፡፡ እርሱንም በተግባር መተርጎም ነው፡፡ በዚህም ምእመናን በሁለቱም ዓለም መመራትን ስኬትንና መልካሙን ሁሉ ያገኛሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከኔም የኾነ መሪ ቢመጣላችሁ መሪየን የተከተለ አይሳሳትም አይቸገረምም፡፡ ከግሳጼዬም የዞረ ሰው ለርሱ ጠባብ ኑሮ አልለው፡፡» (ጧሃ 123-124)