በአላህ ስሞችና ባህሪያት ማመን (ስድስቱ የእምነት መሠረቶች)

ይህ ማለት፥ አላህ በመፅሐፉ ውስጥ ወይም መልእክተኛው በስሱናቸው ያፀደቁትንና አላህ እራሱን የሰየመበትን ስም እንዲሁም ማንነቱን የገለፀበትን ባህሪ ለአላህ በሚገባው መልኩ ማመን ማለት ነው፡፡

ከጉድለት የጠራ የሆነው አላህ ምርጥ የሆኑ ስሞችና ሙሉዕ የሆኑ ባህሪያት አሉት፡፡ በስሙም ሆነ በባህሪያቱ ፍፁም አምሳያ የሌለው ጌታ ነው፡፡ እንዲህ ይለናል “የሚመስለው ምንም ነገር የለም እርሱም ሰሚው ተመልካቱ ነው፡፡” (አል-ሹራ፥11)

አላህ በሁሉም ስሞቹና ባህሪያቱ ከየትኛውም ፍጡር ጋር ፍፁም የማይመሳሰልና የጠራ ነው፡፡

ከአላህ ስሞች ውስጥ የተወሰኑት፡-

አላህ እንዲህ ይላል “እጅግ በጣም ርኀሩኀ በጣም አዛኝ” (አል-ፋቲሐህ፡3)

አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡” (አል ሹራ፡11)(አል ሹራ 11)

አላህ እንዲህ ይላል “እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡” (ሉቅማን፡9) አላህ እንዲህ ይላል “አላህ ከርሱ በቀር ሌላ አምላከ የለም፤ ሕያው ራሱን ቻይ ነው፤” (አል-በቀራህ፡ 255)

አላህ እንዲህ ይላል “ምስጋና ለአላህ ይገባው የዓለማት ጌታ ለሆነው፡፡” (አል-ፋቲሐህ፡2)

በአላህ ስሞችና ባህሪያት የማመን ፍሬዎች፡-

  1. ኃያሉ አላህን ያሳውቀናል፡- በአላህ ስሞችና ባህሪያት ያመነ ሰው ስለ አላህ ያለው እውቀት ይጨምራል፡፡ በአላህ ላይ ያለው እርግጠኛ እምነትም ይጨምራል፡፡ ስለ አላህ አንድነት ያለው ዕምነት ይጠነክራል፡፡ የአላህን ስሞችና ባህሪያት ያወቀ ሰው፥ ቀልቡ በአላህ ታላቅነት፣ ውዴታና አክብሮት መሞላቱ የግድ ነው፡፡

  2. አላህን በስሞቹ ማወደስ እንችላለን፡፡ ይህ ምርጥ ከሆኑ የዚክር (የውዳሴ) ዓይነቶች ውስጥ ይካተታል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል… “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ብዙ ማውሳትን አውሱት፡፡” (አል-አሕዛብ፡ 41)

  3. ስምና ባህሪውን ካወቅን፥ በስሞቹና በባህሪያቱ ልንማፀነው አንችላለን፡፡ አላህ እንዲህ ይላል “ለአላህም መልካም ስሞች አሉት ስትፀልዩም በርሷም ጥሩት” (አል-አዕራፍ፡ 180)በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፡- አንተ ሲሳይን ሰጪ ሆይ! ሲሳይን ስጠኝ፡፡ አንተ ይቅር ባይ ሆይ! ይቅር በለኝ፡፡ አንተ አዛኝ ሆይ! እዘንልኝ… ማለት እንችላለን፡፡

ከፍ ያሉ የእምነት ደረጃዎች፡-

እምነት የተለየዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ የአንድ ሙስሊም እምነት መዘንጋቱንና ሐጢአቱን መነሻ አድርጎ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ለአላህ ባለው ታዛዥነት፣ አምልኮና ፍራቻ ልክ እምነቱ ይጨምራል፡፡

የእምነት ከፍተኛው ደረጃ ሸሪዓው እንዳለው «ኢህሣን» በሚል ይተወቃል፡፡ ስለ «ኢህሣን» ምንነት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል… “አንተ ባታየው እንኳ እርሱ ያይሃልና፥ አላህን ስትገዛው እያየኸው እንደምትገዛው ሆነህ ተገዛው፡፡” (አል-ቡኻሪ፡50 ሙስሊም፡8)

ቆመህም ሆነ ተቀምጠህ፣ በደስታም ሆነ በሃዘን ወቅት በአጠቃላይ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ሆነህ አላህን ማስታወስ ይኖርብሃል፡፡ አላህ ምንግዜም በቅርበት ይመለከትሃል፡፡ እየተመለከተህ መሆኑን ካወቅህ ወንጀል አትፈፅምም፡፡ እርሱ ካንተ ጋር መሆኑን የምታውቅ ከሆነ ፍርሃትም ሆነ ተስፋ መቁረጥ አይቆጣጠሩህም፡፡ በእርግጥ አላህን በሶላትህና በዱዓህ አያናገርከው ብቸኝነት ሊሰማህ አይችልም፡፡

የሰወርከውንም ግልፅ ያደረግከውንም አላህ እንደሚየውቅ እየተገነዘብክ ነፍስህ ወደ ኃጢአት ልትገፋፋህ አትችልም፡፡ኃጢአት ላይ ተዳልጠህና ተሳስተህ ከወደቅህ ደግሞ ወደ አላህ በመመለስ ምህረቱን ትማፀነዋለህ እርሱም ይምርሃል፡፡

አላህን የማመን ፍሬዎች፡-

  1. አላህ ክፉ ነገሮችን ሁሉ ለምእመናን ይከላከልላቸዋል፡፡ ከጭንቅ ያድናቸዋል፡፡ ከጠላቶቻቸው ሴራም ይጠብቃቸዋል፡፡ አላሀ እንዲህ ይላል “አላህ ከነዚያ ካመኑት ላይ ይከላከልላቸዋል፡፡” (አል-ሐጅ ፡ 38)

  2. በአላህ ላይ የሚኖረን እምነት መልካም የሆነን ህይወት፣ ደስታንና ፍስሃን ያጎናፅፋል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል … “ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤” (አል-ነሕል፡97)

  3. እምነት ነፍስን ከከንቱ እምነቶች ፅዱ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው፥ ጉዳዩን ሁሉ ለአንድ አላህ ብቻ ይተዋል፡፡ እርሱ የዓለማት ጌታ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው፡፡ ከርሱ ሌላ እውነተኛ አምላክ የለም፡፡ በአላህ የሚያምን ሰው ፍጡርን አይፈራም፡፡ ማንንም ሰው በቀልቡ አይከጅልም፡፡ ከዚህም በላይ ከንቱና አላስፈላጊ ከሆኑ እምነቶች ራሱን ነፃ ያደርጋል፡፡

  4. የኢማን ከፍተኛ ተፅዕኖ፡- የአላህን ውዴታ ያስገኛል፡፡ ጀነት ያስገባል፡፡ ቋሚና ዘላለማዊ ለሆነ የፀጋ ስኬት ያበቃል፡፡ ሙሉ የአላህ እዝነትን ያስገኛል፡፡