በወንድና በባዕድ ሴት መካከል የሚኖር ግንኙነት ስርዓት

በወንድና በባዕድ ሴት መካከል የሚኖር ግንኙነት ስርዓት

  1. ዓይንን መስበር
 

አንድ ሙስሊም የሌላ ሰውን ሀፍረተ ገላ ማየት አይፈቀድለትም፡፡ የፍቶት ስሜቱን የሚቀሰቅሱ ነገሮችንም መመልከትም የተከለከለ ነው፡፡ ያለ ጉዳይ አንዲትን ሴት አተኩሮ ማየት የለበትም፡፡ አላህ ሱ.ወ) ሁለቱንም ጾታዎች ዓይናቸውን ሰበር እንዲያደርጉ አዟቸዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ የጥብቅነትና የጨዋነት ጎዳና በመሆኑ ነው፡፡ ዓይንን ያለ ገደብ እንደፈለጉ መልቀቅ የዝሙትና የወንጀል መንገድ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ለምዕመናን ንገራቸው ዓይኖቻቸውን ያልተፈቀደን ከማየት ይከልክሉ፤ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ ይህ ለነሱ የተሻለ ነው፤ አላህ በሚሰሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡ ለምእመናትም ንገራቸው ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፡፡›› (አል ኑር 30-31)

በድንገት የተከለከለን ነገር ለማየት የተጋለጠ ሰው ወዲያው ከዚያ እይታ ዓይኑን ሰበር ማድረግ አለበት፡፡ ዓይንን መስበር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በኢንተርኔት ከሚሰራጩ የተከለከሉ ነገሮችንም ያካትታል፤ የፍትወት ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ነገሮችን መመልከት ክልክል ነው፡፡

  1. በስርዓትና በመልካም ስነምግባር አብሮ መኖር

ስርዓትን በጠበቀና መልካም ስነ ምግባርን በተላበሰ መልክ፣ ከማንኛውም ስሜት ቀስቃሽ ነገሮች ርቀው አንዲት ባዕድ ሴትን ቢያናግር፣ እሷም ብታናግረው፣ ማሕበራዊ ሕይወታቸውን ቢመሩ አይከለከልም፡፡

  • አላህ(ሰ.ወ) ሴቶች ባዕድ ወንዶችን ሲያናግሩ ድምፃቸውን እንዳያስለመልሙ ከልክሏል፡፡ ግልጽ የሆነ ንግግርን እንዲናገሩም አዟል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያ በልቡ በሽታ ያለበት እንዳይከጅል በንግግር አትለስልሱም መልካምንም ንግግር ተናገሩ፡፡›› (አል አሕዛብ 32)
  • ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ አረማመዶች፣ እንቅስቃሴዎችና ከጌጦችም ከፊሎቹን ግልጽ ማድረግ የተከለከሉ ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ሴቶችን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ከጌጦቻቸው የሚሸፍኑት ይታወቅ ዘንድ በእግሮቻቸው አይምቱ፡፡›› (አል ኑር 31)
  1. የኸልዋ (ለብቻ መነጠል) እርምነት

ኸልዋ ማለት አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ማንም በማያያቸው ስፍራ ላይ ለብቻቸው መገኘት ሲሆን ይህንን ኢስላም እርም አድርጎታል፡፡ ምክንያቱም፣ ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ፣ ዝሙትና ፀያፍ ተግባራት እንዲፈፀሙ የሚያደርግበት የሸይጣን መግቢያ በር በመሆኑ ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አድምጡ! ከእይታ በራቀ ቦታ ላይ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር አይነጠልም ሦስተኛቸው ሰይጣን ቢሆን እንጂ፡፡›› (አል ቲርሚዚ 2165)

  1. አል ሒጃብ (የሴቶች ኢስላማዊ አለባበስ)

አላህ (ሱ.ወ) በሴቶች ላይ ሂጃብን ግዳጅ ያደረገው ማራኪ ውበትና አታላይ ተክለ ሰውነት ያላበሳቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯቸው ደግሞ ለወንዶች ፈታኝነቱ፣ ወንዶች ለሴቶች ካላቸው ተፈጥሯዊ ፈታኝ ገጽታ በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

 አላህ (ሱ.ወ) ሂጃብን የደነገገው ለብዙ ዓላማ ነው፡

  • ሴት የተፈጠረችለትን ዓላማና የተጣለባትን ማህበረሰባዊ ኃላፊነት፣ በዕውቀትም በተግባርም በብቃትና በጥራት እንድትወጣ እንዲሁም ክብሯንና ጨዋነቷን ጠብቃ እንድትኖር ለማድረግ ነው፡፡
  • የዋልጌነትና የጋጠወጥነት መንስኤዎችን በመቀነስና በማዳከም በአንድ በኩል የማህበረሰቡን ጽዱዕነት በሌላም በኩል የሴትን ክብር ለማስጠበቅ ነው፡፡
  • ወደሴቶች ለሚመለከቱ ወንዶች በጥብቅነትና ስሜትን በመቆጣጠር ላይ ማገዝ፤ ይኸውም እንደማንኛውም የእድገትና የልማት አጋር ከሴቶች ጋር እንዲረዳዱና እንዲተጋገዙ ያደርጋል፡፡ የቅጽበታዊ ስሜት ማርኪያ የፍቶት ስሜት ቀስቃሽ ብቻ አድርገው እንዳይመለከቷት ለማድረግ ያስችላል፡፡