በደልና የሰዎችን ገንዘብ አላግባብ መውሰድ

በደልና የሰዎችን ገንዘብ አላግባብ መውሰድ

መጠኑ ቢያንስም የሰዎችን ገንዘብ በግፍ መውሰድ ከከባባድ ሃጢአቶችና ወንጀሎች መካከል ነው፡፡

በደል ኢስላም ካስጠነቀቃቸው እኩይ ተግባራት መካከል አንዱ ነው፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በደል የትንሳኤ ቀን ጽልመት ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 23215 / ሙሲሊም 2579) ትንሽ ቢሆንም፣ የሰዎችን ገንዘብ ያለ አግባብ መውሰድ ክልክል ነው፡፡ ይህ አላህ(ሱ.ወ) ፈፃሚዎቹን በመጨረሻው ዓለም ላይ ጠንካራ ቅጣት እንደሚገጥማቸው ከወዲሁ በመንገር ከዛተባቸው ከከባባድ ሃጢኦቶችና ወንጀሎች መካከል ነው፡፡ ነብዩ ሰ.ዐ.ወ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ ስንዝር ያክል መሬት የበደለ ሰው በትንሳኤ ቀን ከሰባቱ ምድር (በአንገቱ) ይጠለቅለታል፡፡›› (አልቡኻሪ 2321 /ሙስሊም 1610)

 

በማህበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ ከሚከሰቱ የበደል ምሳሌዎች፡

  1. ማስገደድ፡ በየትኛውም የማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ፣ ማስገደድና በኃይል ማንበርከክ አይፈቀድም፡፡ በነፃ ምርጫና በስምምነት ካልሆነ በስተቀር በማስገደድ የሚፈፀም ማንኛውም ውል ተቀባይነት የለውም፡፡ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሽያጭ (የሚፀድቀው) በስምምነት ነው፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 2185)
  2. የሰዎችን ገንዘብ በሐሰት ለመብላት ማታለልና ማጭበርበር፡ ይህም ከከባባድ ወንጀሎች መካከል ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እኛን ያታለለ ከኛ አይደለም፡፡›› (ሙስሊም 101) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን ሐዲስ የተናገሩበት ምክንያቱ፡ በአንድ ወቅት ወደገበያ ወጣ ባሉበት፣ እህል የያዘ ከረጢት ተመለከቱ፤ ከዚያም እጃቸውን ወደታች ዘለቅ አድርገው በከረጢቱ ውስጥ ሲሰዱት ከታች እርጥበትን አገኙ፤ ወዲያውም ለሻጩ ‹‹አንተ ባለ እህል ይህ ምንድነው?›› አሉት፤ እሱም፡ ‹‹ዝናብ አግኝቶት ነው የአላህ መልክተኛ›› አላቸው፤ እሳቸውም፡- ‹‹ሰዎች እንዲያዩት ከላይ አታደርገውም ነበር? እኛን ያታለለ ከእኛ አይደለም፡፡›› አሉት፡፡ (አል ቲርሚዚ 1315)
  3. የሰዎችን ገንዘብ ያለ አግባብና በግፍ ለመውሰድ በሕግና ደንብ መቀለድ፡ አንድ ሰው የርሱ ያልሆነ ገንዘብን በሕጋዊ መንገድና በፍርድቤት አስወስኖ የመውሰድ ጮሌነትና ፍጥነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የአንድ ዳኛ ፍርድ ስህተትን እውነት ሊያደርገው አይችልም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እኔ የሰው ልጅ ነኝ፤ እናንተ ደግሞ እኔ ዘንድ በመምጣት ትካሰሳላችሁ፤ ምናልባት አንዳችሁ ማስረጃ ከማቅረብ አኳያ ከሌላኛው የበለጠ ይሆንና በሰማሁት መሰረት ለርሱ ልፈርድለት እችላለሁ፡፡ እናም ከወንድሙ መብት ለርሱ የፈረድኩለት ሰው እንዳይወስድ፤ እኔ ለርሱ የቆረጥኩለት ከእሳት የሆነ ቁራጭን ነውና፡፡››
  4. ጉቦ ማለት፣አንድ ሰው የርሱ ያልሆነን ንብረት ለማግኘት ሲል ገንዘብ ወይም የሆነ አገልግሎት መስጠቱ ሲሆን፣ ይህ ተግባር ከበደል ዓይነቶች ሁሉ አደገኛው በደልና ከባዱ ወንጀል ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጉቦ ሰጪውንም ተቀባዩንም ረግመዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 1337) በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ጉቦ ከተስፋፋ፣ ስርዓት የለሽነት ይሰፍናል፤ ስርዓት ይንኮታኮታል፡፡ እድገቱና ስልጣኔውም ይቆማል፡፡

በካሃዲነቱ ዘመን ያለ አግባብ ገንዘብ ይወስድ የነበር ሰው ኢስላምን ሲቀበል ፍርዱ ምንድነው?

አንድ ሰው አግባብ ባልሆኑ መንገዶች በግፍ ድንበር በማለፍ በስርቆት ወይም በመሸወድና ወዘተ ከሰዎች የወሰደው ገንዘብ እሱ ዘንድ እያለ ከሰለመ የሚያውቃቸው ከሆነና ምንም ዓይነት አደጋ ሳይከሰት ለነርሱ ማስረከብ የሚችል ከሆነ ለባለቤቶቹ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡

ይህን ገንዘብ፣ ምንም እንኳን ኢስላምን ከመቀበሉ በፊት ያገኘው ቢሆንም ይህ በግፍ ድንበር በመተላለፍ የተወሰደ ገንዘብ በእጁ ያለ ገንዘብ ነው፡፡ እናም ከቻለ ይህን ገንዘብ መመለስ ይገባዋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድታደርሱ ያዛችኋል፡፡›› (አል ኒሳእ 58)

ባለቤቱን ለማወቅና ለማግኘት የሚችለውን ያክል ከጣረ በኋላ ማወቅ ካልቻለ ገንዘቡን በመልካም ስራዎች ላይ በማዋል መጽዳት አለበት፡፡