በጎ መዋልና ለጋስነት – ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል

ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል፡

 ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በስነ ምግባራቸው ከሰዎች ሁሉ የላቁ ነበሩ

 

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ እጅግ የላቀ ለሆነው የሰው ልጅ መልካም ስነ ምግባር ዓይነተኛ ተምሳሌት ነበሩ፡፡ ቁርኣን የሳቸውን ስነ ምግባር ታላቅ በማለት የገለጸው ለዚህ ነው፡፡ ባለቤታቸው እመት ዓኢሻም(ረ.ዐ) ስለርሳቸው ስነ ምግባር ሲናገሩ፡- ‹‹ስነ ምግባራቸው ቁርኣን ነበር፡፡›› ከማለት ሌላ የተሻለ የረቀቀ አገላላጽ አላገኙለትም፡፡ እርሳቸው፣ ለቁርኣን ስነ ምግባራዊ አስተምሮት ተግባራዊ ተምሳሌት ነበሩ፡፡

በጎ መዋልና ለጋስነት፡

  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመልካም ነገር ላይ ለጋስ ሰው ነበሩ፡፡ እጅግ በጣም ለጋስ የሚሆኑት ደግሞ በረመዳን ወር፣ ጅብሪል(ዐ.ሰ) በሚጎበኛቸው ጊዜ ነው፡፡ በረመዳን ውስጥ፣ ረመዳን እስከሚያልቅ ድረስ በየሌሊቱ ጅብሪል(ዐ.ሰ) ይጎበኛቸው ነበር፡፡ በዚህም ጉብኝቱ ቁርኣንን ያናብባቸዋል፡፡ እናም ጅብሪል(ዐ.ሰ) በሚጎበኛቸው ጊዜ ለመልካም ነገር ያላቸው ለጋስነት ወይም ፈጣንነት ከተላከ ንፋስ የፈጠነ ነበር፡፡ (አል ቡኻሪ 1803 / ሙስሊም 2308)
  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተጠይቀው ያልሰጡት ነገር የለም፡፡ አንድ ጊዜ፣ የሆነ ሰው ሊጠይቃቸው መጥቶ፣ በሁለት ተራሮች መሐል ያለን ሸለቆ የሚሞሉ ፍየሎችን ሰጡት፤ እናም ሰውየው ወደ ጎሳዎቹ በመመለስ፣ «ሕዝቦቼ ሆይ ስለሙ፤ ሙሐመድ ድህነትን የማይፈራ የሆነን ስጦታን ይሰጣል፡፡» አለ፡፡ (ሙስሊም 2312)
  • በአንድ ወቅትም ሰማንያ ሺህ ዲርሃም መጣላቸውና በከረጢት አስቀመጡት፤ ከዚያም ተመልሰው መጡና አከፋፈሉት፤ አንድንም ለማኝ ሳይመልሱ ሁሉንም አከፋፍለው ጨረሱ፡፡ (አል ሃኪም 5423)
  • አንድ ሰው ወደሳቸው በመምጣት ጠየቃቸውና፡ ‹‹ምንም የምሰጥህ ነገር የለኝም፤ ቢሆንም በኔ ስም ግዛና የሆነ ነገር ከመጣልኝ እከፍለዋለሁ፡፡›› ሲሉት፣ ዑመር(ረ.ዐ) «አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ፣ አላህ የማይችሉትን ነገር አላስገደደዎትም»- ለምን እራሶዎን ያስጨንቃሉ- ሲላቸው፣ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የዑመር(ረ.ዐ) አስተያየት አላስደሰታቸውም ነበር፤ ሰውየውም እንዲህ አለ፡ «ስጥ የዙፋኑ ባለቤት እንደሆነ ያሳንስብኛል ብለህ አትፈራ፡፡» አላቸው፤ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) በሰውየው ንግግር ፈገግ አሉ፡፡ የደስታ ስሜት በፊታቸው ላይ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ (አል አሓዲሱል ሙኽታራ 88
  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሑነይን ዘመቻ በተመለሱ ጊዜ የገጠር ሰዎችና አዲስ ሙስሊሞች ከተገኘው ምርኮ ስጦታ ከጅለው ወደሳቸው መጡ፤ በጣም አጨናነቋቸውም፤ በጣም ከማጨናነቃቸው የተነሳ ወደ ዛፍ ስር አስጠጓቸው፤ የዛፉ ቅርንጫፍ ልብሳቸውን ገፈፋቸው፤ በዚህን ጊዜ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡- ‹‹ልብሴን ስጡኝ፤ በነዚህ ዛፎች ቅርንጫፍ ልክ ገንዘብ ቢኖረኝ እንኳን በመካከላችሁ አከፋፍዬው፣ ከዚያም ስስታምም ሆነ ውሸታም፣ እንዲሁም ድህነትን ፈሪ እንዳልሆንኩኝ ታውቁ ነበር፡፡›› አሉ፡፡ (አል ቡኻሪ 2979)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ የአላህ እዝነትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁንና በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ውስጥ የመልካም ስነ ምግባር ዓይነተኛ ተምሳሌት ነበሩ፡፡