በጦርነት ላይ ያለው የኢስላም ስነ ምግባራዊ መመሪያ

በጦርነት ላይ ያለው የኢስላም ስነ ምግባራዊ መመሪያ

  1. ኢስላም ከጠላት ጋር ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነት እንዲኖር አዟል፤ በደልንና በነርሱ ላይ ድንበር ማለፍን ከልክሏል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፤ አስተካክሉ፤ እርሱ (ማስተካከል)ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡›› (አል ማኢዳ 8) ለጠላቶቻችሁ ያላችሁ ጥላቻ ድንበር እንድታልፉና በደል እንድትፈጽሙ ሊያደርጋችሁ አይገባም ማለት ነው፡፡ ይልቁንም በንግግራችሁም ሆነ በተግባራችሁ ፍትሃዊ ሁኑ እያለ ነው፡፡
  2. ኢስላም፣ ከጠላት ጋር በሚደረግ ውልና ስምምነት መክዳትንና ማታለልን ይከለክላል፡፡ ጠላትንም ቢሆን መክዳትና ማታለል ክልክል ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አላህ ከዳተኞችን አይወድምና፡፡›› (አል አንፋል 58)
  3. ኢስላም የጠላትን ሬሳ ማንገላታትና መቆራረጥን ይከለክላል፡፡ የሙታንን ገላ መቆራረጥ ሐራም ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡-‹‹ሬሳን አትቆራርጡ›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 1731)
  4. በጦርነት ላይ የማይሳተፉ አካባቢን በማበላሸት የማይታወቁ የሆኑ ሰላማዊ ነዋሪዎችን መግደል ይከለክላል ታላቁ ሠሐቢይ፣ የሙስሊሞች ኸሊፋ፣ አቡበከር(ረ.ዐ)፣ ኡሳማ ቢን ዘይድን(ረ.ዐ) ወደ ሻም ሀገር የጦር መሪ አድርገው በላኩ ጊዜ፡- ‹‹ታዳጊ ሕፃንን፣ ያረጀ ሽማግሌንም፣ ሴትንም አትግደሉ፡፡ የተምር ዛፍን አትቁረጡ አታቃጥሉም፡፡ የሚያፈራ ዛፍንም አትቁረጡ፡፡ ልትመገቡ ካልሆነ በስተቀር በበቀል የሕዝቦችን ፍየሎች፣ ላምና ግመሎች አትረዱ፡፡ እራሳቸውን ለአምልኮ ያገለሉ፣ በገዳማት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ያጋጥሟችኋል፤ እራሳቸውን አሳልፈው በሰጡለት ነገር ላይ ተዋቸው፡፡›› ብለዋል፡፡ (ኢብኑ ዓሳኪር 2/ 50)