ቤተሰብን መጣራት (ወደ ኢስላም መጣራት)

አላህ ኢስላምን እንዲቀበል የቸረው ሰው፣ ቤተሰቦቹንና የቅርብ ዘመዶቹን ወደ ኢስላም የመጥራት ከፍተኛ ጉጉት ሊያድርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ከማንም በላይ ለርሱ ቅርቦቹና ወዳጆቹም በመሆናቸው ነው፡፡ ለዚህም ከነርሱ የሚደርስበትን ስቃይና እንግልት በትግስት ማሳለፍ አለበት፡፡ የተለያዩ በብልሃት የተሞሉ መንገዶችን መጠቀም ይኖርበታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-

‹‹ቤተሰብህንም በስግደት እዘዝ፤ በርሷም ላይ ዘውትር፡፡›› (ጧሃ 132) አንዳንድ ሰዎች በሚያደርጉት ዳዕዋ ባዕድ ሲቀበላቸው ቤተሰባቸውና የቅርብ ዘመዳቸው ግን እንቢተኛ ሲሆን እንመለከታለን፡፡ በዚህም እጅግ ይበሳጫሉ፤ ተስፋም ይቆርጣሉ፡፡ ነገር ግን ስኬታማ ዳዕዋ አድራጊ፣ የዳዕዋ ስልቶችንና አካሄዶችን በመቀያየር በተለያየ መንገድ ዳዕዋ በማድረግ የሚታገልና ዳዕዋ ለሚያደርግላቸው ሰዎች አላህ(ሱ.ወ) እንዲመራቸው የሚማጸንላቸው የሆነ ሰው ነው፡፡ እልህ አስጨራሽ በሆኑ አጋጣሚዎች ላይም ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከአጎታቸው አቡ ጣሊብ ጋር የነበራቸውን ታሪክ ብንመለከት፣ አጎታቸው ይረዳቸው፣ ይደግፋቸው፣ ከቁረይሾችም ጥቃት ይከላከልላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢስላምን አልተቀበለም፤ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) እርሱን ወደ ኢስላም በመጥራት የሚያደርጉትን ሙከራ እስከመጨረሻው እስትንፋሱ ድረስ አላቋረጡም፡፡ በዚያ ቅጽበት ላይ ሆኖ፡- ‹‹አጎቴ ሆይ ላኢላሃ ኢለላህ በል፤ አላህ ዘንድ የምሞግትልህ የሆነችን ቃል በል፡፡›› አሉት፡፡ (አል ቡኻሪ 3671/ ሙስሊም 24) ነገር ግን ለርሳቸው ጥሪ ምላሽ ሳይሰጥ በክህደት ላይ ሞተ፤ አላህም የሚከተለውን አንቀጽ አወረደ፤ ‹‹አንተ የወደድከውን ሰው ፈጽሞ አታቀናም፤ ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል፤ እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው፡፡›› (አል ቀሠሥ 56 ) አንድ ዳዕዋ የሚያደርግ ሰው የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ሃይማኖቱን የማሰራጨትና ሰዎችን ወደ መልካም ነገር የመምራት ግዴታ አለበት፡፡ ልቦች በአላህ እጅ ናቸው፤ የሻውን ወደ ቀጥተኛው መንገድ ይመራል፡፡