ተፈጥሯዊ ፈለጎች

ተፈጥሯዊ ፈለጎች

ተፈጥሯዊ ፈለግ ምን ማለት ነው?

 ኢስላም አንድ ሙስሊም ባማረ ግርማ ሞገስ ላይ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡

ተፈጥሯዊ ፈለግ ማለት አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅን የፈጠረበት መገለጫዎች ማለት ነው፡፡ አንድ ሙስሊም እነኚህን ነገሮች በመፈፀሙ ሙሉዕ የሚሆንባቸው ናቸው፡፡ ይህን በማድረጉ ያማረ ገጽታና የተዋበ ግርማ ሞገስ ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ኢስላም እነኚህን የውበትና የቁንጅና መሰረት የሆኑ ጉዳዮችን ልዩ ትኩረት በመስጠት አንድ ሙስሊም ውጫዊና ውስጣዊ ማንነቱም ያማረ እንዲያደርግ አዟል፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አምስት ነገሮች ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ናቸው፤ መገረዝ፣ በብልት ዙሪያ የሚበቅልን ጸጉር መላጨት፣ ቀድሞ ቀመስን ማሳጠር፣ ጥፍርን መቁረጥ፣ እና በብብት ስር ያለን ጸጉር መንጨት፡፡›› (አል ቡኻሪ 5552/ ሙስሊም 257)

ግርዛት፡ ይህ በብልት ጫፍ ላይ የሚገኝ ቆዳን ማስወገድ ወይም መቁረጥ ነው፡፡ በተለምዶ ይህ ቆዳ እንዲወገድ የሚደረገው በመጀመሪያዎቹ የአራስነት ቀናት ነው፡፡

ግርዛት ለወንዶች ተወዳጅና ከተፈጥሯዊ ፈለጎች መካካል ነው፡፡ ከጤናም አንጻር በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ነገር ግን ወደ ኢስላም ለመግባት መስፈርት አይደለም፡፡ አንድ ሙስሊም ፈርቶ ወይም በሌላ ምክንያት ባይገረዝ ወንጀለኛ አይሆንም፡፡

ኢስቲሕዳድ፡ ይህ በብልት ዙሪያ ያለን ጸጉር መላጨት ወይም በፈለገው መንገድ ማስወገድ ነው፡፡

ቀድሞ ቀመስን ማሳጠር፡ ቀድሞ ቀመስን ባለበት መተው የተፈቀደ ቢሆንም የተወደደ ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድ ሙስሊም ቀድሞ ቀመሱን ከተወው እጅግ በጣም እስኪረዝም ድረስ መተው የለበትም ሊከረክመውና ሊያሳጥረው ይገባል፡፡

ጺምን ማሳደግ፡ ኢስላም ጺም ማሳደግን ያበረታታል፡፡ ጺም የሚባለው በአገጭና በጉንጮች ላይ የሚበቅል ጸጉር ነው፡፡

ጺምን ማሳደግ ማለት ባለበት መተውና አለመላጨት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ መከተል ነው፡፡

ጥፍርን ማስተካከል፡ አንድ ሙስሊም የጥፍሩን እድገትና ንጽህና ሊከታተል ይገባዋል፡፡ የቆሻሻ መከማቺያ እንዳይሆን በየጊዜው በማሳጠር ማስተካከል አለበት፡፡ የብብትን ጸጉር መንጨት፡ አንድ ሙስሊም፣ በብብት ስር ያለውን ጸጉር በመንጨት ወይም በሌላ ማሰወገጃ ዘዴ በመጠቀም ማስወገድ አለበት፡፡ ይህም ከርሱ መጥፎ ጠረን እንዳይወጣ ለመከላለከል ይረዳዋል፡፡