አል ሒጃብ (የሴቶች ኢስላማዊ አለባበስ)

አል ሒጃብ (የሴቶች ኢስላማዊ አለባበስ)

አላህ (ሱ.ወ) በሴቶች ላይ ሂጃብን ግዳጅ ያደረገው ማራኪ ውበትና አታላይ ተክለ ሰውነት ያላበሳቸው በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯቸው ደግሞ ለወንዶች ፈታኝነቱ፣ ወንዶች ለሴቶች ካላቸው ተፈጥሯዊ ፈታኝ ገጽታ በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

 አላህ (ሱ.ወ) ሂጃብን የደነገገው ለብዙ ዓላማ ነው፡

  • ሴት የተፈጠረችለትን ዓላማና የተጣለባትን ማህበረሰባዊ ኃላፊነት፣ በዕውቀትም በተግባርም በብቃትና በጥራት እንድትወጣ እንዲሁም ክብሯንና ጨዋነቷን ጠብቃ እንድትኖር ለማድረግ ነው፡፡
  • የዋልጌነትና የጋጠወጥነት መንስኤዎችን በመቀነስና በማዳከም በአንድ በኩል የማህበረሰቡን ጽዱዕነት በሌላም በኩል የሴትን ክብር ለማስጠበቅ ነው፡፡
  • ወደሴቶች ለሚመለከቱ ወንዶች በጥብቅነትና ስሜትን በመቆጣጠር ላይ ማገዝ፤ ይኸውም እንደማንኛውም የእድገትና የልማት አጋር ከሴቶች ጋር እንዲረዳዱና እንዲተጋገዙ ያደርጋል፡፡ የቅጽበታዊ ስሜት ማርኪያ የፍቶት ስሜት ቀስቃሽ ብቻ አድርገው እንዳይመለከቷት ለማድረግ ያስችላል፡፡

የሂጃብ ይዘት

አላህ (ሱ.ወ) ሴት ልጅ በባዕድ ወንዶች ፊት ከፊቷና ከመዳፎቿ በስተቀር ሰውነቷን በሙሉ እንድትሸፍን ግዴታ አድርጓል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ጌጣቸውንም ከርሷ ግልጽ የኾነውን በስተቀር አይግለጡ፡፡›› (አል ኑር 31)

ግለጽ የኾነ የሚባለው ፊትና መዳፍን ነው፤ እሱም ቢሆን፣ ፊትና መዳፍን በመገለጥ የሚከሰት ፈተና ወይም ችግር ካለ መሸፈናቸው ግድ ይሆናል፡፡

የሒጃብ ስርዓተ ደንብ

አንዲት ሴት የሚከተሉትን ቅድመ መስፈርቶች በጠበቀ መልክ የፈለገችውን ዓይነት መልክና ይዘት ያለው ሒጃብ ወይም ልብስ መልበስ ይፈቀድላታል፡፡

  1. ሒጃቡ የግድ መሸፈን ያለበትን የሰውነት ክፍል በጠቅላላ የሚሸፍን መሆን አለበት
  2. ሰፊ መሆን አለበት፤ የሚያጣብቅ፣ ጠባብ፣ የሰውነትን ቅርጽ የሚያወጣና የሚያሳይ መሆን የለበትም፡፡
  3. ወፍራም መሆን አለበት፡፡ ስስነቱ በስሩ ያለን የሰውነት ክፍል የሚያጋልጥና የሚያሳይ መሆን የለበትም፡፡