አምልኮ ማለት ምን ማለት ነው?

አምልኮ ማለት ምን ማለት ነው?

አምልኮ (ኢባዳ) ማለት፡- አላህ የሚወደውና የሚደሰትበት እንዲሁም ንግግሮችንና ተግባራትን ሁሉ የሚያጠቃልል ስም ሲሆን ሰዎች ይተገብሩት ዘንድ አላህ ያዘዘው ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር እንደ ሶላት፣ ዘካ፣ ሐጅ ግልፅ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ አላህንና መልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) እንደ መውደድ፣ አላህን እንደ መፍራት፣ በርሱ እንደመመካትና ከርሱ እርዳታን እንደመፈለግ ስውር ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎችም አንደዚሁ፡፡

 

በሁሉም የሀይወት ዘርፍ አላህን ስለማምለክ፡-

ወደ አላህ መቃረብን ዓላማው ያደረገ የማንኛውም አማኝ ሙእሚን ተግባር በአምልኮ ዒባዳ ውሰጥ ይካተታል፡፡ በእስልምና ሃይማኖት መሠረት አምልኮ በሶላት፣ በፆምና በመሳሰሉ የፀሎት ስነ-ሥርዓቶች የተገደበ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም ማንኛውም ዓይነት ጠቃሚ ተግባር መልካም የሆነን ዓላማ (ኒያ) እስካነገበ ድረስ፥ የአምልኮ ተግባር እንደሆነ የሚቆጠር ሲሆን ተግባሪውም አላህ ዘንድ ይመነዳበታል፡፡ የአላሀ ትዕዛዝ በአግባቡ ለመፈፀም ይቻል ዘንድ አካላዊ ጥንካሬ ለማግኘት በሚል ዓላማ አንድ ሙስሊም ቢመገብ፣ ቢጠጣና ቢተኛ አላህ ዘንድ ምንዳ ያገኝበታል፡፡ ስለዚህ ሙስሊም ህይወቱን በሙሉ ለአላህ እያስገዛ ነው ማለት ነው፡፡ አላህን ለመታዘዝ ሰውነቱ ይጠነክር ዘንድ ይመገባል፡፡ በዚህ ዓላማ በመመገቡ አላህን እያመለከ ነው፡፡ ከአመንዝራነት ራሱን ለመጠበቅ በሚል ዓላማ ትዳር ይመሰርታል፡፡ ጋብቻው በራሱ የአምልኮ ተግባር ይሆንለታል፡፡ ልክ እንደዚሁ ዓላማው ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ ንግዱ፣ ሥራው፣ ቢዝነሱ ሁሉ አምልኮ ይሆንለታል፡፡ እውቀት መፈለጉ፣ መመራመሩ፣ መፈላሰፉ፣ መፍጠሩ ሁሉ እንደ አምልኮ ይቆጠርለታል፡፡ አንዲት እንስት ባልዋን፣ ልጆቿንና ቤቷን መንከባከቧ በርሱ የአምልኮ ተግባር ይሆንላታል፡፡ በሁሉም የህይወት ዘርፍ የሚከናወኑ ጠቃሚ ተግባራት በሙሉ መልካም ዓላማና ዕቅድን መነሻ አድርገው እስከተፈፀሙ ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ይቆጠራሉ፡፡

አምልኮ (ዒባዳ) ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ነው፡-

አላህ እንዲህ ይላል… “ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ ከነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም፤ ሊመግቡኝም አልሻም፡፡ አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው፡፡” (አል- ዛሪያት፡56-58)

አላህ ሰውንም ሆነ ጋኔን የፈጠረበት ጥበብ እርሱን ይግገዙ ዘንድ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ እነዚህ ፍጥረታት አላህን የሚግገዙት ለራሳቸው ጥቅም እንጂ አላህ ከእነርሱ ጥቅም ፈላጊ ሆኖ አይደለም፡፡

ሰው የተፈጠረበትን መለኮታዊ ይህን ዓላማ ዘንግቶ በዓለማዊ ህይወት ውስጥ ሰጥሞ ከቀረ፥ በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ፍጥረታት የሚለየው ምንም ነገር አይኖርም ማለት ነው፡፡ እንስሳቶች ከሰው በተቃራኒ በቀጣዩ ዓለም ስለሰሩት ሥራ አይጠየቁም እንጂ እነርሱም ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይፈነጥዛሉ፡፡ አላህ እንዲህብሏል… “… እነዚያም የካዱት (በቅርቢቱ ዓለም) ይጠቀማሉ፤ እንስሳዎችም እንደሚበሉ ይበላሉ እሳትም ለነርሱ መኖሪያቸው ናት፡፡” (ሙሐመድ፡12) ተግባርና ዓላማቸው ከእንስሳ ጋር ተመሳስሏል፡፡ ነገርግን ከእንስሳ የሚለያቸው በመጨረሻው ቀን የስራቸውን ውጤት ማግኘታቸው ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም ምንም ከማያውቁት እንስሳት በተለየ አዕምሮ ያላቸው፣ የሚገነዘቡና የሚያውቁ በመሆናቸው ነው፡፡

የአምልኮ (ዒባዳ) መሠረቶት

አላህ እንተገብረው ዘንድ ያዘዘን አምልኮ በሁለት ዋና ዋና መሠረቶች ላይ የተገነባ ነው፡-

አንደኛ፡- ሙሉ የሆነ ፍራቻና መተናነስ፡-

ሁለተኛ፡- ሙሉ የሆነ ውዴታን ለአላህ ማዋል፡-

አላህ በባሮቹ ላይ ግዴታ ያደረገው አምልኮ፥ ለአላህ ብቻ የሚውል ሙሉ የሆነ ፍራቻ፣ መተናነስና ዝቅ ማለትን በውስጡ ያካተተ ከመሆኑ ጎን ለጎን ሙሉ የሆነ ውዴታና ክጃሎትን ለአላህ ብቻ ማዋልን ይጠይቃል፡፡

ስለሆነም ልክ ምግብን ወይም ገንዘብን እንደምንወደው ሁሉ አላህንም ፍራቻና መተናነስን ባላካተተ አኳኋን የምንወደው ከሆነ አምልኮ አይባልም፡፡ ልክ እንደዚሁ አውሬና ጨቋኝ መንግስትን እንደምንፈራው ሁሉ አላህንም ውዴታን ባላጎዳኘ አኳኋን የምንፈራው ከሆነ ከአምልኮ አይቆጠርም፡፡ ሆኖም ግን በስራችን ውስጥ ውዴታንና ፍራቻን ካቆራኘን ትክክለኛ አምልኮን አስገኝተናል፡፡ አምልኮ ደግሞ ሊውል የሚገባው ለአላህ ብቻ ነው፡፡

የአምልኮ ቅድመ ሁኔታዎች፡-

አምልኮ የተስተካከለና አላህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርበታል፡፡

 

የመጀመሪያው አምልኮን ያለ ምንም ተጋሪ ለአላሀ ብቻ ማዋል ሲሆን

ሌላው ደግሞ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከአከናወኑት የአምልኮ ተግባር ጋር የሚጣጣምና የሚስማማ መሆን ይኖርበታል፡፡

አላህ እንዲህ ብሏል “አይደለም እርሱ በጎ ሰሪ ሆኖ ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው ለርሱ በጌታው ዘንድ ምንዳው አለው፤ በነርሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነሱም አያዝኑም፡፡” (አል-በቀራህ፡112) በዚህ አንቀፅ ውስጥ “ፊቱን ለአላህ የሰጠ ሰው” ማለት፥ የአላህን አንድነት በተግባር ያረጋገጠና አምልኮን ለርሱ ብቻ ያጠራ ማለት ነው፡፡ “በጎ ሰሪ ሆኖ” የሚለው ደግሞ፥ የአላህን ህግና የመልእክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ.) አርዓያነት የሚከተል ማለት ነው፡፡

ሥራን ከመልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ.) ሱንና (መንገድ) ጋር ማጣጣም ማለት እንደ ሶላት፣ ፆምና አላህን ማውሳት የመሳሰሉት ተግባራትን እርሳቸው ባከናወኑት መሠረት መፈፀም ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ሌሎች የዕለት ተዕለት ተግባራትን ለጥሩ ዓላማ (ኒያ) እስካከናወናቸው ድረስ ከአምልኮ ተግባራት ተርታ የሚመደቡ ቢሆንም፥ ከአላህ መልእክተኛ ሱንና ጋር የግድ እንዲጣጣሙ ማድረግ አይጠበቅብንም፡፡ ባይሆን መጠንቀቅ የሚኖርብን ሸሪዓውን የሚቃረን ሐራም ነገር ላይ ላለመውደቅ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የአላህን ትዕዛዝ ለመተግበር ጠንካራ ያደርገው ዘንድ ስፖርት ቢሰራ ወይም የቤተሰቡንና የልጆቹን ወጪ ለመሸፈን ስራ ቢሰራ ኒያውን እስካሳመረ ድረስ እንደ አምልኮ ተግባር ቢቆጠርለትም ከሱንና ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ግዴታ አይደለም፡፡