አስካሪ መጠጥና አልኮል

አስካሪ መጠጥና አልኮል

ማንኛውም አዕምሮን የጋረደ ወይም ከርሱ ተቀላቅሎ ያሸነፈው ወይም ሸፍኖት ተጽእኖ ያሳደረበት ነገር በሙሉ ኸምር ወይም አስካሪ መጠጥ ነው፡፡ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ማንኛውም አስካሪ ነገር ኸምር ነው፡፡ ማንኛውም ኸምር ደግሞ ሐራም ነው፡፡›› (ሙስሊም 2003) አስካሪ መጠጡ፣ እንደ ወይን፣ የቴምር እሸት፣ በለስና ዘቢብ ባሉ ፍራፍሬዎች፣ አለያም እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ ወይም ሩዝ ባሉ አዝርዕቶች፣ ወይም እንደ ማር ባሉ ጣፋጭ ነገሮች የተሰራ ቢሆንም ፍርዱ አንድ ዓይነት ነው፡፡ ማንኛውም አዕምሮን የጋረደ ነገር፣ በየትኛውም ስም ቢጠራም በየትኛውም መንገድ ቢዘጋጅም ኸምር ነው፡፡ ከጭማቂዎች ጋር ወይም ከጣፋጮችና ቸኮሌቶች ጋር ተቀላቅሎ የተዘጋጀ ቢሆንም እንኳኸምር ነው፡፡

 ኢስላም አዕምሮን ከሚረብሹትና ከሚጎዱት ነገሮች ሁሉ ጠብቆታል፡፡

አዕምሮን መጠበቅ

ይህ ታላቅ ሃይማኖት፣ በቅርቢቱም ሆነ በወዲያኛው ዓለም የባሮችን ጥቅም በማረጋገጥና በማስጠበቅ ላይ ትኩረት የሰጠ ሃይማኖት ነው፡፡ ከነዚህም ጥቅሞች መካከል እጅግ አንገብጋቢና አስፈላጊ ለሆኑ አምስት ነገሮች ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ አድርጎላቸዋል፡፡ እነሱም ሃይማኖት፤ ነፍስ፤ አዕምሮ፤ንብረትና ዘር ናቸው፡፡

አዕምሮ የኃላፊነት መሰረት ነው፡፡ የሰው ልጅ መለኮታዊ ክብርና ምርጫን የተጎናጸፈበት አካል ነው፡፡ በመሆኑም ኢስላማዊው ድንጋጌ እርሱን ከሚያበላሽና ከሚያዳክም ማናቸውም ነገር ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ አድርጎለታል፡፡

የኸምር ፍርድ

ኸምር መጠጣት ከከባባድ ወንጀሎች መካከል የሆነ ወንጀል ነው፡፡ በቁርኣንና በነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ሐዲሶች ላይ የኸምርን እርምነት የሚያውጁና የእሷን ጉዳይ አጥብቀው የሚያወግዙ መልክቶች ተላልፈዋል፡፡ ከነኚህም መካከል፡

  • አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ የሚያሰክር መጠጥ፣ ቁማርም፣ ጣኦትም፣ አዝላምም፣ ከሰይጣን ስራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው፡፡ (እርኩስን) ራቁትም ልትድኑ ይከጀላልና፡፡›› (አልማኢዳ 90) አላህ (ሱ.ወ) ኸምርን የገለጻት በነጃሳነቷ ነው፡፡ የሰይጣን ተግባር መሆኗን ከገለጸም በኋላ መዳን የምንፈልግ ከሆነ ከእርሷ እንድንርቅም አዞናል፡፡
  • ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ማንኛውም አስካሪ መጠጥ ኸምር ነው፡፡ ማንኛውም ኸምር ደግሞ ሐራም ነው፡፡ በዱንያ ላይ ኸምርን የጠጣና እሱን አዘውታሪ ሆኖ የሞተ በአኼራ አይጠጣም፡፡›› (ሙስሊም 2003)
  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ኸምር መጠጣት ከኢማን ጋር የሚቃረንና እሱን የሚያጓድል እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድም ሰው በሚጠጣበት ቅጽበት ላይ ሙእሚን ኾኖ ኸምርን አይጠጣም፡፡›› (አል ቡኻሪ 5256 / ሙስሊም 57)
  • ኢስላም ኸምርን በሚጠጣ ሰው ላይ ቅጣትን በይኗል፡፡ ኸምርን የሚጠጣ ሰው ክብሩ ይጎድፋል፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ ታማኝነቱ ይወገዳል፡፡
  • በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) እስከሚሞት ድረስ ኸምርን በመጠጣት ላይ የዘወተረንና በመሰል ተግባር ላይ የተሰማራን ሰው አሳማሚ ቅጣት እንደሚጠብቀው ዝቷል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ (ሱ.ወ) የሚያሰክርን ነገር የሚጠጣ ሰውን የመግል እንጥፍጣፊን ሊያጠጣው ቀጠሮ ዝቶበታል፡፡›› (ሙስሊም 2002) ይህ መግል የጀሀነም ሰዎች ቁስል እዥ ነው፡፡
  • ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ኸምርን በመጠጣት ላይ የተሳተፈም ሆነ የረዳ ሰው በዛቻው ውስጥ ይካተታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በኸምር ዙሪያ ተሳታፊና ተያያዥነት ያላቸውን አስር ሰዎች ረግመዋል፡፡ ጠማቂውን፣ አስጠማቂውን፣ ጠጪውን፣ ተሸካሚውን፣ አሸካሚውን፣ ቀጂውን፣ ሻጩን፣ ዋጋውን የሚበላውን፣ እሱን ገዝቶ ጋባዡን፣ እና የሚገዛለትን ወይም ተጋባዡን ረግመዋል፡፡ (አል ቲርሚዚ 1295)