አንድ ሰው ወደ ኢስላም እንዴት ሊገባ ይችላል?

አንድ ሰው ወደ ኢስላም እንዴት ሊገባ ይችላል?

አንድ ሰው ሁለቱን የእምነት የምስክርነት ቃል ትርጉማቸውን አውቆ፣ በልቦናውም እርግጠኛ ሆኖ፣ በምላሱ በመናዘዝ ወደ ኢስላም ይገባል፡፡ እነኚህ ሁለት የእምነት የምስክርነት ቃሎች የሚከተሉት ናቸው፡

  1. «ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚገዙት አምላክ አለመኖሩን እመሰክራለሁ» ይላል፡፡ ከአላህ ባሻገር በእውነት የሚገዙት አምላክ እንደሌለ በልቦናዬ አምኜ በምላሴ እመሰክራለሁ፤ እርሱን በብቸኝነት አመልካለሁ፤ ለርሱ አጋር የለውም ማለት ነው፡፡
  2. «ሙሐመድ የአላህ መልክተኛ ናቸው ብዬ እመሰክራለሁ» ይላል፡፡ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)፣ ወደ ሰው ልጆች ሁሉ የተላኩ የአላህ መልክተኛ መሆናቸውን በልቦናዬ አምኜ በምላሴ እመሰክራለሁ፤ ላዘዘው ነገር ታዛዥ፣ ለከለከለውም ተከልካይ እሆናለሁ፤ አላህንም ከርሱ ድንጋጌና ፈለግ ጋር በሚገጥም መልኩ እገዛለሁ፤ ማለት ነው፡፡ (ገጽ፣ 40-48 ተመልከት)

አዲስ ሙስሊም ገላውን ይታጠባል

የሰው ልጅ፣ ወደ ኢስላም የገባበት ቅጽበት በሕይወቱ ውስጥ ከባድ ቦታ ያለው አጋጣሚ ነው፡፡ እውነተኛው ልደቱ ያ ነው፡፡ በሕይወት የመገኘቱን ሚስጥር የሚረዳው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ሃይማኖት ውስጥ ከመግባቱ ጋር ተያይዞ ሰውነቱን በጠቅላላ በውሃ መታጠብ ይኖርበታል፡፡ ውስጡን ከማጋራትና ከወንጀሎች እንዳጠራና እንዳጸዳ ሁሉ ላዩንም በውሃ በመታጠብ ቢያጸዳ ይወደድለታል፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አንድ ከዐረብ መኳንንት መካከል የነበረን ሠሐብይ ወደ ኢስላም ለመግባት በፈለገ ጊዜ ሰውነቱን እንዲታጠብ አዘውት ነበር፡፡ (አል በይሃቂ 837)