ኢስላም ዓለም አቀፍ ሃይማኖት

ኢስላም ዓለም አቀፍ ሃይማኖት፡-

የእስልምና ሃይማኖት የተደነገገው፥ በተለያየ ባህል፣ ዘር፣ ልምድና ሃገር ውስጥ ለሚኖሩ ሁሉም ዓይነት ሕዝቦች ዕዝነትና የህይወት ጎዳና ይሆን ዘንድ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል…«(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማት እዝነት አድርገን እንጂ አላክንህም» (አል-አንቢያ፡107)

ለዚህ ነው የእስልምና ሃይማኖት የማንኛውንም ሕዝብ ባህልና ልምድ የሚያከብረው፡፡ የእስልምናን መሠረታዊ ህግጋት የማይጥስ እስከሆነ ድረስ አዲስ ሰለምቴዎች የነበሩበትን ባህልና ልምድ እንዲተው አይገደዱም፡፡

እስልምናን በግልፅ የሚቃረን ልምድና ባህል ከሆነ ግን፥ ከሀይማኖቱ ጋር ተስማሚ በሆነ ባህል መለወጥ ግድ ይላል፡፡ ከጉድለታት የጠራው ኃያሉ አላህ አንድን ነገር የሚከለክለውም ሆነ የሚያዘው ጥልቅና ውስጥ ዐዋቂነቱን መነሻ አድርጎ ነው፡፡ ለአላህ ህግጋት ተገዥ መሆናችን፥ በርሱ የማመናችን መገለጫ ነው፡፡

እዚህ ጋር አንድ ማሳሰብ የሚኖርብን ነገር ይኖራል፡፡ ይኽውም አንድ አዲስ ሰለምቴ የሆነ ሰው፥ ከእስልምና እና ከሕግጋቶቹ ጋር አንዳችም ግንኙነት የሌላቸው ባሕላዊ ልምዶችን አንዳንድ ሙስሊሞች ሲያከናውኑ አይቶ ይህንኑ ለመተግበር መፈለጉ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ መሰሉ ተግባር ሃይማኖት ሳይሆን በልምድ የተያዘና የተፈቀደ የየዕለት ባህል መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል፡፡

መሬት ሁሉ አላህን የማምለኪያ ቦታ ነው፡-

በኢስላም አተያይ የትኛውም የመሬት ክፍል ለመኖርም ሆነ አላህን ለማምለክ የተፈቀደና ምቹ ነው፡፡ ሙስሊሞች ተሰደው ይኖሩበት ዘንድ ግዴታ የተጣለባቸው ውሱን የሆነ ሃገርም ሆነ ቦታ የለም፡፡ ዒባዳ ለማድረግ እስከቻሉ ድረስ በየትኛውም ሃገር መኖር ይችላሉ፡፡

አንድ ሙስሊም ዒባዳ እንዳያደርግ የሚከለክለው ኃይል እስካልገጠመው ድረስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይሰደድ ዘንድ አይገደድም፡፡ አላህን ከማምለክ የሚያግደው ከአቅም በላይ የሆነ ሐይል ካጋጠመው ግን ዒባዳ ማድረግ ወደ ሚችልበት ሌላ ቦታ መሰደድ ይኖርበታል፡፡ አላህ እንዲህ ይላል…«እናንተ ያመናችሁ ባሮች ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ (ብትቸገሩ ተሰደዱ) እኔንም ብቻ ተገዙኝ፡፡» (አል-ዐንከቡት፡56)