ኢስላም የህይወት ሃይማኖት

ኢስላም የህይወት ሃይማኖት

የእስልምና ሃይማኖት የዚህን ዓለም (ዱንያ) ህይወትና የቀጣዩን ዓለም (አኼራ) ህይወት አመዛዝኖ ጎን ለጎን የሚያስኬድ ሃይማኖት ነው፡፡ ዱንያ ዘር የመዝሪያ ዓለም ነው፡፡ አንድ ሙስሊም በዚህም ሆነ በቀጣዩ ዓለም የዘራውን ለማጨድ፥ በሁሉም የህይወት ዘርፍ መልካም የተባሉ ነገሮችን ሁሉ የሚተክለው በዚህ የዱንያ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ ይህንን ተክልና ዘር አግባብነት ባለው መልኩ ለመዝራትና ለመትከል፥ ህይወትን በቆራጥ ውሳኔና በፅናት ማስተናገድን ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁኔታ እንደሚከተለው ሊገለፅ ይችላል፡፡

ምድርን ማልማት

አላህ እንዲህ ይላል «… እርሱ ከምድር ፈጠራችሁ፤ በውስጧ እንድታለሟትም አደረጋችሁ፡፡» (ሁድ፡61) አላህ የዚህ ምድር ነዋሪዎች እንሆን ዘንድ ፈጥሮናል፡፡ እንድናለማት፣ አንድናሳድጋትና እንድናበለፅጋትም አዞናል፡፡ ገር የሆነውን ኢስላማዊ ሸሪዓ በማይቃረን መልኩ ለሰው ልጅ ግልጋሎት ትውል ዘንድ መገንባት እንዳለብንም አዞናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከባድ ሁኔታ ባጋጠመህ ወቅት እንኳ ምድርን ማልማትና ማሳደግ የአምልኮ ተግባር (ዒባዳ) እንደፈፀምክ ይቆጠርልሃል፡፡ ለዚህ ነው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.)፥ አንድ ሰው ችግኝ ለመትከል በእጁ ይዞ ሳለ ቂያማ ብትቆም እንኳ፥ እስከ ቻለ ድረስ ሰደቃ ይሆንለት ዘንድ የያዛትን ችግኝ ይትከላት በማለት ያስገነዘቡት፡፡ (አል-ሙሰነድ፡ 2712)

ከሰዎች ጋር መኗኗር

የእስልምና ሃይማኖት ምድርን በመገንባቱና በማበልፀጉ ረገድ ከሰዎች ጋር እንድንተጋገዝ ያበረታታናል፡፡ የየሰው ባህልና ሃይማኖት የተለያየ ቢሆንም መልካም ሥነ-ምግባርና ሰናይ የሆነ ግብረ-ገብነትን በመላበስ ተቀላቅለን እንድንኗኗርና እንድንተባበር ሃይማኖቱ ያዘናል፡፡ ከህብረተሰቡ ተነጥሎ መኖርና መገለል፥ የከሀዲዎችና የለውጥ አራማጆች መንገድ አለመሆኑንም ያስገነዝበናል፡፡ ይህ በመሆኑ ነበር የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከሰዎች ጋር አብረው ይኖሩ የነበረውና የሚያደርሱባቸውን ሁከትና ማዋከብም በፀጋ እንዲሁም በትዕግስት ያስተናግዱ የነበረው እንዲህ አይነቱ ሰው ከሚነጠለውና ከሚገለለው ሰው የተሻለ ነውም ይሉ ነበር፡፡ (ኢብን ማጃህ፡ 4032)

የዕውቀት ሃይማኖት

 ኢስላም እንደ ሌሎች ሃይማኖቶች በሃይማኖትና በእውቀት መካከል የሚደረግን ጦርነት አያውቅም

በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ላይ የወረደው የመጀመሪያው የአላህ ቃል «አንብብ!» የሚለው መሆኑ እንዲሁ እንደዘበት የተከሰተ ክስተት አይደለም፡፡ ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑ የዕውቀት ዘርፎች ሁሉ በእስልምና ሃይማኖት የተበረታቱ ናቸው፡፡

ሌላው ቀርቶ አንድ ሙስሊም ዕውቀት ለመቅሰም ሲንቀሳቀስ ወደ ጀነት በሚያደርሰው ጎዳና ላይ እየተጓዘ መሆኑን ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ብለዋል…«እውቀት በሚያስገበይ ተግባር ላይ የተሰማራ ሰው በዚህ ጥረቱ አላህ ወደ ጀነት የሚያደርሰውን ጎዳና ገር ያደርግለታል፡፡» (ኢብን ሒባን ፡ 84)

ሌሎች ሃይማኖቶች እንደሚያስቡት የእስላም ሃይማኖት በዕውቀትና በሃይማኖት መካከል ግጭት አለ ብሎ አያምንም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በተቃራኒው ሃይማኖት ዕውቀትን ማፈላለጊያ ብርሃን ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለሰው ልጅ እስከጠቀመ ድረስ ማወቅና ማሳወቅ ተገቢ ተግባር መሆኑን እስልምና ያስገነዝባል፡፡

እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖት፥ ለሰዎች መልካም ነገርን የሚያስተምር አዋቂና አስተማሪ ደረጃው እጅግ ከፍ ያለና የተከበረ መሆኑን ይናገራል፡፡ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ፍጥረታት በጠቅላላ ለሰዎች መልካምን ነገር ለሚያስተምር ግለሰብ እንደሚፀልዩ (ዱዓእ) እንደሚየደርጉ ተናግረዋል፡፡ (ቲርሚዚ ፡ 2685)