እዝነት – ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል

ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በስነ ምግባራቸው ከሰዎች ሁሉ የላቁ ነበሩ

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ እጅግ የላቀ ለሆነው የሰው ልጅ መልካም ስነ ምግባር ዓይነተኛ ተምሳሌት ነበሩ፡፡ ቁርኣን የሳቸውን ስነ ምግባር ታላቅ በማለት የገለጸው ለዚህ ነው፡፡ ባለቤታቸው እመት ዓኢሻም(ረ.ዐ) ስለርሳቸው ስነ ምግባር ሲናገሩ፡- ‹‹ስነ ምግባራቸው ቁርኣን ነበር፡፡›› ከማለት ሌላ የተሻለ የረቀቀ አገላላጽ አላገኙለትም፡፡ እርሳቸው፣ ለቁርኣን ስነ ምግባራዊ አስተምሮት ተግባራዊ ተምሳሌት ነበሩ፡፡

እዝነት፡

  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አዛኞች አርረህማን ያዝንላቸዋል፤ በምድር ውስጥ ላለ እዘኑ፤ ከሰማይ በላይ ያለው ያዝንላችኋልና፡፡›› ብለዋል (አል ቲርሚዚ 1924 / አቡ ዳውድ 4941)

የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አዛኝነት በበርካታ ስፍራዎች ላይ ይንጸባረቃል፤ ከነዚህም መካከል፡

ለሕፃናት የነበራቸው እዝነት፡

  • አንድ ገጠሬ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ መጣና፡ «ልጆቻችሁን ትስማላችሁን? እኛ ግን አንስማቸውም፡፡» አላቸው፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ)፣ ‹‹ታዲያ አላህ ከቀልብህ ውስጥ እዝነትን የነጠቀ ከሆነ እኔ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?›› በማለት መልስ ሰጡት፡

(አል ቡኻሪ 5652 ሙስሊም 2317) ሌላ ገጠሬ ደግሞ የዓሊይን ልጅ ሐሰንን ሲስሙ ተመለከታቸውና፣ «እኔ አስር ልጆች አሉኝ ነገር ግን አንዱንም ስሜው አላውቅም፡፡» አለ፡፡ በዚህን ጊዜ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹እነሆ የማያዝን አይታዘንለትም፡፡›› አሉት፡ (ሙስሊም 2318)

  • አንድ ጊዜ የልጃቸውን ሴት ልጅ፣ ኡማማ ቢንት ዘይነብን ይዘው ሰግደዋል፡፡ ሱጁድ ሲያደርጉ ቁጭ ያደርጓታል፤ ሲቆሙም ይሸከሟት ነበር፡፡ (አል ቡኻሪ 494/ ሙስሊም 543)
  • ሠላት ውስጥ ሆነው የሕፃን ልጅ ለቅሶ ከሰሙ፣ ሠላቱን አጠርና ፈጠን አድርገው ይሰግዱ ነበር፡፡ አቡ ቀታዳ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡ ‹‹ሠላት ስሰግድ በውስጧ ማስረዘምን እፈልጋለሁ፤ ከዚያም የሕፃን ልጅ ለቅሶ እሰማለሁ፤ እናም እናትየዋን እንዳላስጨንቃት በማሰብ ሠላቴን አሳጥራለሁ፡፡›› (አል ቡኻሪ 675/ ሙስሊም 470)

ለሴቶች የነበራቸው እዝነት

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሴት ልጆችን በመንከባከብ ለነርሱ በጎ በመዋል ላይ አነሳስተዋል፡፡ ‹‹በነዚህ ሴት ልጆች የሆነ ፈተናን የተፈተነ ለነርሱም በጎን የዋለ ሰው ለርሱ ከእሳት ግርዶ ይሆኑለታል፡፡›› ይሉም ነበር፡፡

(አል ቡኻሪ 5649 / ሙስሊም 2629)

የሚስትን መብት በተመለከተ ጠበቅ አድርገዋል፡፡ የሷን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ቸረውታል፡፡ የተለየ እንክብካቤም ሰጥተውታል፡፡ ሙስሊሞችም በዚሁ ዙሪያ ከፊላቸው ለከፊሉ አደራን እንዲያስተላልፍ አዘዋል፡፡ ‹‹ ስለ ሴቶች መልካም ነገርን ተናዘዙ፡፡›› ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 4890)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከቤተሰባቸው ጋር ገራገር በመሆን ዓይተኛ ተምሳሌት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት ግመላቸው አጠገብ ቁጭ ባሉበት ባለቤታቸው ሠፊያ(ረ.ዐ) እግሯን በጉልበታቸው ላይ በማድረግ ተንጠላጥላ ግመሉ ላይ ወጥታለች፡፡ (አል ቡኻሪ 2120) ልጃቸው ፋጢማ እሳቸው ዘንድ በምትመጣ ጊዜ እጇን ይዘው ይስሟታል፤ እርሳቸው በሚቀመጡበት ቦታም ያስቀምጧታል፡፡ (አቡ ዳውድ 5217)

ለደካሞች የነበራቸው እዝነት

 ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶችና ለችግረኞች በጎ የሚውልን ሰው፣ በአላህ መንገድ ላይ ከሚታገል ሰው ጋር እኩል አድርገውታል፡፡ .

  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ ሰዎች ወላጅ አልባ ሕፃናትን የመንከባከብ ኃላፊነትን እንዲወስዱ ያነሳሱ ነበር፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- አመልካች ጣታቸውንና የመሐል ጣታቸውን በማቆራኘት፣ – ‹‹እኔና ወላጅ አልባ ሕፃንን (የቲምን) የሚንከባከብ ሰው፣ በጀነት ውስጥ እንዲህና እንዲህ ነን›› ብለዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 4998)
  • ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች እና ለችግረኞች ጉዳይ የሚሯሯጥና የሚለፋን ሰው፣ ቀኑን በጾም፣ ሌሊቱን ደግሞ በመስገድ ከሚያሳልፍ፣ በአላህ መንገድ ላይ ከሚታገል ታጋይ ጋር እኩል አድርገውታል፡፡ (አል ቡኻሪ 5661/ ሙስሊም 2982)
  • ለደካሞች መራራትና መደንገጥ፣ መብታቸውን መጠበቅ ወይም መስጠት፣ ለሲሳይ መጨመርና በጠላት ላይ ድልን የመጎናጸፊያ ሰበብም እንደሆነ አስተምረዋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹ደካሞችን ፈልጉልኝ፤ ድልን የምታገኙትም ሆነ ሲሳይን የምታገኙት በደካሞቻችሁ ነው፡፡›› ይላሉ፡፡ (አቡ ዳውድ 2594)

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለእንሰሳት የነበራቸው እዝነት

  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ ሰዎች ለእንሰሳት እንዲራሩ ያሳስቡ ነበር፡፡ የማይችሉትን ነገር እንዳያሸክሟቸውና እንዳያንገላቷቸው አስጠንቅቀዋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ (ሱ.ወ) በነገሮች ሁሉ አሳምሮ መስራትን ደንግጓል፤ እናም ስትገድሉ አገዳደላችሁን አሳምሩ፤ ስታርዱም አስተራረዳችሁን አሳምሩ፤ አንዳችሁ ቢላዋውን ይሳለው፤ እርዱንም በቶሎ ያሳርፈው ፡፡›› (ሙስሊም 1955)
  • አንድ ሠሐብይ እንዲህ ብሏል፡- በአንድ ወቅት ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ያቃጠልነውን የጉንዳን መንደር ተመለከቱና፣ ‹‹ይሄን ያቃጠለው ማን ነው?›› በማለት ጠየቁ፤ እኛ ነን አልናቸው፤ እሳቸውም፡ ‹‹የእሳት ጌታ እንጂ በእሳት ማንም ማንንም ሊቀጣ አይገባም፡፡›› አሉን፡፡ (አቡ ዳውድ 2675)