ከወንድ አንጻር ሴቶች ያላቸው ስፍራ

ከወንድ አንጻር ሴቶች ያላቸው ስፍራ

ሴት ለወንድ ከምትሆንለት አንጻር በብዙ ክፍል ትመደባለች፡

  1. ሴቷ ለወንዱ ሚስት መሆኗ

አንድ ወንድ ሚስቱን በፈለገው መልኩ ማየትና በሷ መርካት ይፈቀድለታል፡፡ ሴትም ከባሏ ጋር እንዲሁው ይፈቀድላታል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የመንፈስ ትስስራቸውን፣ የስሜት ውህደታቸውንና የአካል ቅርርባቸውን ሲገልጽ፣ ባልን የሚስት ልብስ ሚስትንም የባል ልብስ በማለት ይገልጻቸዋል፡፡ ‹‹እነርሱ ለናንተ ልብሶች ናቸው፤ እናንተም ለነርሱ ልብሶች ናችሁ፡፡›› (አል በቀራ 187) (ገጽ፣ 204 ተመልከት)

  1. የቅርብ ዘመዱ (መሕረም) ከሆነች

ከሴቶች መሕረም የሚባሉት፣ አንድ ወንድ ፈፅሞ ሊያገባቸው የማይችሉ የሆኑ ሴቶች ናቸው፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡

1 ወላጅ እናትና አያት፤ አያትነቱ ቢረዝምም ቢያጥርም አንድ ነው፡፡
2 የራሱን ሴት ልጅ፣ የወንድ ልጁ ሴት ልጅ፣ የሴት ልጁ ሴት ልጅ፤ የልጅ ልጅነታቸው ምንም ያክል ቢወርድም እርምነቱ ያው ነው፡፡
3 የእናት አባቱ ልጅ እህቱ፣ በአባት የሚገናኙ እህቱ፣ ወይም በእናት የሚገናኙ እህቱ፤
4 የአባቱ እህት አክስቱ፤ ለአባቱ እህትነቷ በአባትም በእናትም ቢሆንም በአባት ብቻ ወይም በእናት ብቻም ቢሆንም ልዩነት የለውም፡፡ የአባት አክስትና የእናት አክስትም በዚሁ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡
5 የእናቱ እህት የሹሜው፤ ለእናቱ እህትነቷ በአባትም ሆነ በእናትም ቢሆን፣ በአባት ወይም በእናት ብቻም ቢሆን ልዩነት የለውም፡፡ የአባት አክስትና የእናት አክስትም በዚሁ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡
6 የወንድሙ ሴት ልጅ፤ ወንድምነቱ በእናትም በአባትም፣ ወይም በእናት ብቻ፣ ወይም በአባት ብቻ ቢሆንም ልዩነት የለውም፡፡
7 የወንድም ወንድ ልጅ ሴት ልጅን ይመስል የልጅነት ሐረጓ ቢወርድም ፍርዱ ያው ነው፡፡
8 የሚስቱ እናት፡ ሚስቱ አብራው ብትሆንም ወይም ቢፈታትም እናቷ እስከመጨረሻው መሕረምነቷ ይቆያል፡፡ ልክ እንዲሁ የሚስት እናት እናት ወይም የሚስት አያትም ከዚሁ ትመደባለች፡፡
9 ከርሱ የማትወለድ የሚስቱ ሴት ልጅ
10 የልጅ ሚስት ወደ ታች የሚወለድ ቢሆንም ለምሳሌ እንደ ልጅ ልጅ ሚስት
11 ወደ ላይ ከፍ ቢልም የአባት ሚስት ወይም ልክ እንደ የልጅ ሚስት በአባት በኩል
12 የጡት እናቱ፡ የጡት እናት ማለት በሁለቱ የመጀመሪያ የአራስነት ዓመታት ወቅት ውስጥ አምስት ጊዜ ጠግቦ የጠባት ሴት ናት፡፡ እርሱን በማጥባቷ ምክንያት ኢስላም ለርሷ በርሱ ላይ መብት ደንግጎላታል፡፡
13 የጡት እህቱ፡ ይህች ደግሞ እርሱን ያጠባችው ሴት ልጅ ናት፡፡ በዚሁ መልክ፣የጡት አክስት የጡት ወንድም ልጅ የጡት እህት ልጅና የመሳሰሉት ሁሉም የጡት ዘመዶች ልክ የደም ትስስር እንዳላቸው ዘመዶች እርም ይሆናሉ፡፡
  1. ሴቷ ለርሱ ባዕድ ከሆነች

ባዕድ ሴት የምትባለው ከተጠቀሱት መሓሪሞች ውጭ ያለች ሴት ሁሉ ነች፡፡ ከርሱ ጋር ዝምድና ያላቸው ቢሆኑም፣ እንደ አጎት ልጅ፣ የአክስት ልጅ፣ የወንድሙ ሚስት፣ ወይም ከርሱ ጋር ዝምድና የሌላቸው ቢሆንም ከርሱ ጋር የሚያስተሳስራቸው የዘር ሐረግ ወይም የአማችነት ትስስር ባይኖርም በኢስላም እይታ አጅነቢ ወይም ባዕድ ናቸው፡፡

በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከእምነት አስተምህሮ በራቁ ቤተሰቦችና ማህበረሰብ ውስጥ የአስገድዶ መድፈርና ፀያፍ የወንጀል ስራዎች በሰፊው ተስፋፍተዋል፡፡

በእርግጥ ኢስላም አንድ ሙስሊም ከባዕድ ሴት ጋር ሊኖረው የሚገባን ግንኙነት ሥርዓትና መመሪያ አድርጎለታል፡፡ ይህ ደግሞ ክብርን የሚጠብቅና የሰይጣን በሮችን የሚዘጋ ነው፡፡ የሰው ልጅን የፈጠረው አላህ(ሱ.ወ)፣ ለርሱ የሚበጀውን ከማንም በላይ ያውቃል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹የፈጠረ አምላክ እርሱ ዕውቀተ ረቂቁ ውስጥ ዐዋቂው ሲኾን (ሚስጥርን ሁሉ) አያውቅምን?›› (አል ሙልክ 14)