ወደ ቀጥተኛው ጎዳና የመመራትንና የንሠሐን ጸጋ ማመስገን

ወደ ቀጥተኛው ጎዳና የመመራትንና የንሠሐን ጸጋ ማመስገን

አንድ ሙስሊም አላህ(ሱ.ወ) በርሱ ላይ ከዋላቸው ጸጋዎች ታላቁ የሆነውን፣ ወደ ቀጥተኛው ጎዳና የመመራትንና የንሠሐን ጸጋ ከሚያመሰግንባቸው መንገዶች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. ሃይማኖትን አጥብቆ መያዝና ለሚያጋጥሙ ችግሮች ታጋሽ መሆን

የድልብ ባለቤት የሆነ ሰው፣ ንብረቱ የወሮበሎችና የዘራፊዎች እጅ እንዳያገኘው ከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበቃ ያደርግለታል፡፡ ለጉዳት ከሚዳርጉት ነገሮች ሁሉ ይከላከለዋል፡፡ ኢስላም ለሰው ዘር በጠቅላላ የተበረከተ ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ የአመለካከት አቅጣጫ ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ሰዎች ባሻቸው ጊዜ የሚፈፅሙት ስሜትም አይደለም፡፡ እያንዳንዱን የሕይወት ገጠመኝና እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርና የሚያስተዳድር ሃይማኖት ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) መልክተኛውን (ሰ.ዐ.ወ) ኢሳላምን፣ የቁርኣንን መመሪያ አጥብቀው እንዲይዙ ያዘዛቸውና በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ማፈግፈግ ሊኖር እንደማይገባ የገለጸላቸው ለዚህ ነው፡፡ ይህም ኢስላም ትክክለኛውና ቀጥተኛው ጎዳና በመሆኑ ነው፡፡

‹‹ያንንም ወዳንተ የተወረደልህን አጥበቀህ ያዝ አንተ በቀጥተኛው መንገድ ላይ ነህና፡፡›› ይላል፡፡ (አል ዙኽሩፍ 43) አንድ ሙስሊም ኢስላምን ከተቀበለ በኋላ በሚያጋጥመው ችግርና መከራ ማዘን የለበትም፡፡ ለችግርና ለመከራ መጋለጥ የአላህ ተፈጥሯዊ ሕግ ነው፡፡ ከኛ በላጭና ታላቅ የነበሩት መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ብርቱ ችግርና መከራ ደርሶባቸው ታግሰዋል፤ ታግለዋል፡፡ የአላህን ነብያት ብንመለከት፣ አላህ ታሪካቸውን ተርኮልናል፤ በምን መልኩ እንደተንገላቱና እንደተሰቃዩ ነግሮናል፤ ከጠላት በፊት የዘመድና የጓደኛ ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጾልናል፤ ሆኖም በአላህ መንገድ ላይ በገጠማቸው ነገር ምንም አልተዳከሙም፤ የነበራቸውን አቋምና እምነት አልቀየሩም አልለወጡም፡፡ ስለዚህ ይህ በአንተም ላይ የደረሰብህ ችግር፣ እምነትህ እውነተኛ፣ እርግጠኛነትህም ጠንካራ በመሆኑ ከአላህ የሆነ ፈተና ነው፡፡ እናም በፈተናው ልክ አንተም በርታ! ይህን ሃይማኖትህን አጥብቀህ ያዝ፤ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በዱዓቸው ላይ በብዛት ይደጋግሙ እንደነበረው አንተም አላህን ለምነው፡ ‹‹አንተ ልብን ገለባባጭ የሆንክ ጌታ ሆይ! ልቤን በእምነትህ ላይ አጽናልኝ፡፡›› በል፡፡ (አል ቲርሚዚ 2140) ይህንኑ በማስመልከት አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሰዎች አምነናል በማለታቸው ብቻ እነሱ ሳይፈተኑ የሚተዉ መኾናቸውን ጠረጠሩን? እነዚያንም ከነሱ በፊት የነበሩትን በእርግጥ ፈትነናል፤ እነዚያንም እውነት የተናገሩትን አላህ በእርግጥ ያውቃል፤ ውሸታሞቹንም ያውቃል፡፡›› (አል አንከቡት 2-3)

  1. በጥበብና በመልካም ግሳፄ ወደ ኢስላም በመጣራት ላይ መታገል

ይህ የሰው ልጅ ለተጎናጸፈው የኢስላም ጸጋ ምስጋና ከሚገለፅባቸው መንገዶች መካከል ትልቁ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአላህ ሃይማኖት ላይ ጽናት እንዲኖር ከሚያደርጉ ምክንያቶችም ዋነኛው ነው፡፡ አንድ ከአደገኛ በሽታ ነፃ የሆነ፣ ሌት ተቀን ሲያንገላታውና ሲያሰቃየው ከነበረው ደዌ ሰውነቱ ጤናማ የሆነለት ሰው፣ እንዲሁም በምን መልኩ ከዚህ በሽታ መገላገያውንና ፍቱን መድሃኒቱን ያወቀ ሰው፣ በሰዎች መሐል ይህን ዕውቀቱን ለማሰራጨት ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጎት ያድርበታል፡፡ በተለይም ለቤተሰቦቹ፣ ለቅርብ ዘመዶቹና ለሚወዳቸው ሰዎች ይህን ማስተማሩ ጥርጥር የለውም፡፡ እንግዲህ በሚከተለው መልኩ የሚብራራው ይህ ነው፡፡