ወደ አላህ መጣራት ያለው ትሩፋት (ወደ ኢስላም መጣራት)

ወደ አላህ መጣራት ትልቅ ችሮታ ካላቸው ስራዎችና ወደ አላህ ከሚያቃርቡ ነገሮች ላቅ ያለው ነው፡፡ ይህንኑ የሚያደንቁና የሚያበረታቱ የቁርኣን አንቀጾችና የሐዲስ ዘገባዎች አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. ወደ አላህ መጣራት በቅርቢቱ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም የመዳኛና የስኬት መንገድ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ከናንተም ወደ በጎ ነገር የሚጠሩ፣ በመልካም ስራም የሚያዙ፣ ከክፉ ነገርም የሚከለክሉ ህዝቦች ይኑሩ፤ እነዚያም እነሱ የሚድኑ ናቸው፡፡›› (አል ዒምራን 104)
  2. የአንድ ወደ ኢስላም ጥሪ አድራጊ ሰው ንግግር አላህ ዘንድ በላጭና ተወዳጅ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የአንድን ተጣሪ ንግግር ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ወደ አላህ ከጠራና መልካምንም ከሰራ፤ እኔ ከሙስሊሞች ነኝ ካለም ሰው ይበልጥ ቃሉ ያማረ ማን ነው?›› (አል ፉሢለት 43) ከርሱ ንግግር የበለጠ ያማረ ንግግር የለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው፣ ሰዎች ጌታቸውን፣ ፈጣሪያቸውን፣ እንዲሁም ከማጋራት ጭለማዎች ወደ ኢማን ብርሃን ያወጣቸውን ጌታቸውን እንዲያመልኩ የሚያመለክትና የሚመራ ሰው ነው፡፡
  3. ጥሪ ማድረግ(ዳዕዋ)፣ የአላህን ትዕዛዝ መፈፀምም ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ወደ ጌታህ መንገድ በብልሃትና በመልካም ግሳጼ (በለዘብታ ቃል) ጥራ፡፡›› (አል ነሕል 125) ስለሆነም አንድ ተጣሪ ወይም ዳዒ ወደ ኢስላም ሲጣራ በብልሃት ሊሆን ይገባል፡፡ ሁሉንም ነገር በቦታው ማኖር አለበት፡፡ ይኸውም ለሚጠራቸው ወገኖች የሚስማሙና አንገብጋቢ የሆኑ ነገሮችን በመምረጥና በማዘጋጀት እንደየደረጃቸው ምክርና ጣፋጭ የሆነ ተግሳጽን መስጠት ነው፡፡ ለዘብ ባለና ገር በሆነ መልኩ ከነርሱ ጋር መወያየትና ለነርሱ መመራት ቅርብ የሆነውን አካሄድ መጠቀም አለበት፡፡
  4. ወደ አላህ መጣራት የመልክተኞች ሁሉ፣ በተለይ የነቢያችን የሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተግባር ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እሳቸውን በሰው ልጆች ላይ መስካሪ አድርጓቸዋል፡፡ ለምእመናን በጀነት አብሳሪ፤ ለካሃዲያንና ለአመጸኞች ከእሳት አስጠንቃቂ አድርጎ ልኳቸዋል፡፡ ወደ አላህ የሚጣሩ በሰው ዘር ውስጥ መለኮታዊ ብርሃንን የሚያሰራጩም ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አንተ ነብይ ሆይ እኛ መስካሪ አብሳሪና አስፈራሪም አድርገን ላክንህ፤ ወደ አላህም በፈቃዱ ጠሪ አብሪ ብርሃንም (አድርገን ላክንህ) አማኞችንም ከአላህ ዘንድ ለነርሱ ታላቅ ችሮታ ያላቸው መኾኑን አብስራቸው፡፡›› (አል አሕዛብ 45-47)
  5. ጥሪ ማድረግ ወይም ዳዕዋ የማይዘጋ የመልካም ነገር በር ነው፡፡ ጥሪህን የተቀበለና በአንተ እጅ የተመራ ሰው ካለ ወይም ከገጠመህ ላንተም የእርሱ ዓይነት ምንዳ አለልህ፡፡ በሠላቱ፣ በአምልኮው፣ ሰዎችን ባስተማረ ቁጥር ላንተም ምንዳው ይጻፍልሃል፡፡ እንዲህ ያለው ተጣሪ የሚያገኘው ጸጋ ምንኛ የላቀ የአላህ ጸጋ ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ወደ ቀጥተኛው ጎዳና የተጣራ ሰው፣ እርሱን ከነርሱ ምንዳ ምንም ነገር ሳይጎድል የተከተሉት ሰዎች ምንዳ ይጻፍለታል፡፡›› (ሙስሊም 2674)
  6. የአንድ ዳዒ ምንዳ ከዱንያና በውስጧ ካሉ መጣቀሚያ ነገሮች ሁሉ የተሻለና የበለጠ ነው፡፡ አንድ ዳዒ ምንዳውን የሚያገኘው ከአላህ ዘንድ ነው፡፡ ከሰዎች የሚጠብቀው ምንም ዓይነት ምንዳ የለም፡፡ ምንዳው ትልቅ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ለጋሱ አላህ ደግሞ ለሚወደው ትልቅን ነገር እንጂ አይሰጥም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በነቢዩላህ ዩኑስ (ዐ.ሰ) አንደበት እንዲህ ይላል፡- ‹‹ብትሸሹም (አትጎዱኝም) ከምንዳ ምንንም አልለምናችሁምና፡፡ ምንዳዬ በአላህ ላይ እንጂ በሌላ ላይ አይደለም፤ ከሙስሊሞች እንድኾንም ታዝዣለሁ፡፡›› (ዩኑስ 72) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድን ሰው አላህ በአንተ ሰበብ ቢመራልህ፣ ቀያይ ግመሎች ላንተ ከሚኖሩህ ይሻላል፡፡›› (አል ቡኻሪ 2847 / ሙስሊም 2406)