የተባረከው የእርድ በዓል

የተባረከው የእርድ በዓል

 በህንድ አገር የሚገኙ ሙስሊሞች የተባረከውን የእርድ በዓል ሠላት ሲሰግዱ

ዒድ አልአድሓ፣ በወርሃ ዙልሒጃ አስረኛ ቀን ላይ የሚከበር ሁለተኛው የሙስሊሞች በዓል ነው፡፡ ይህ ወር በኢስላማዊው ቀመር አስራ ሁለተኛው ወር ነው፡፡ በዚህ ዕለት በርካታ ትሩፋቶች ይገኛሉ፡፡ ከነኚህም ትሩፋቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

  1. ሪያዎቹ አስር ቀናቶች ናቸው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፡-‹‹ከነዚህ አስርት ቀናት ይበልጥ አላህ ዘንድ በውስጣቸው የሚሠሩ መልካም ሥራዎች ተወዳጅ የሚሆኑበት ቀን የለም፡፡›› ብለው ሲናገሩ ባልደረቦቻቸው፣ «በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ትግልም ቢሆን?» በማለት ጠየቁ፤ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አዎን! ነፍሱንና ንብረቱን ይዞ የወጣ፣ ከዚያም አንዱንም ይዞ ያልተመለሰ ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ በአላህ መንገድ ላይ የሚደረግ ትግልም ቢሆን (አይበልጥም) አሉ፡፡ (አል ቡኻሪ 926 / አት ቲርሚዚ 757)
  2. የታላቁ ሐጅ ዕለት ነው፡ በውስጡ ከሐጅ ሥራዎች እጅግ የላቀው፣ አንገብጋቢውና የተከበረው ሥራ ይገኛል፡፡ ያም፣ በካዕባ ዙሪያ መዞር፤ እርድን መፈፀም፤ ጀምረተል ዐቀባ ላይ ጠጠር መወርወርና ሌሎች ተግባራት ይከናወኑበታል፡፡

በእርዱ ቀን(የውመ ነሕር) የሚሠሩ ሥራዎች

ሐጅ ላይ ላልሆነ ሰው፣ በዒድ አልአድሓ ዕለት ከዘካተል ፊጥር ውጭ በጾም ፍች በዓል ላይ የሚተገበሩ ነገሮችን በሙሉ መተግበር ይፈቀድለታል፡፡ ዘካተል ፊጥር(የጾም ፍች ምጽዋት)፣ በጾም ፍቺ በዓል ላይ ብቻ የሚተገበር ነው፡፡ እነኚህን ተግባራት ከዚህ በፊት ጠቅሰናቸዋል፡፡

የእርድ በዓል (ዒድ አልአድሓ)፣ ወደ አላህ መቃረቢያ እርድ (ቁርባን) የሚቀርብበት ዕለት መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡

እርድ(ኡዱሒያ)፡ እርድ(ኡዱሒያ)፣ በእርድ ቀን ከዒድ ሠላት መልስ ወደ አላህ ለመቃረብ የሚሰዋ ወይም የሚታረድ ግመል፣ ከብት፣ ወይም ፍየልና በግ ሲሆን የወርሃ ዙል ሒጃ አስራ ሦስተኛ ቀን ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ሊተገበር ይችላል፡፡ አላህ(ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ስለዚህ ለጌታህ ስገድ (በስሙ) ሰዋም፡፡›› (አል ከውሰር 2) አንቀጹ በዒድ ሠላትና በዒድ ዕለት በሚፈፀሙ እርዶች ተተርጉሟል፡፡

ኢስላማዊ ፍርዱ፡ እርድ፣ በሚችል ሰው ላይ ጠበቅ ያለ ሱና ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ለራሱና ለቤተሰቦቹ ማረድ አለበት፡፡

ለእርድ የሚቀርበው እንሰሳ ማሟላት ያለበት መስፈርት

  1. ከቤት እንሰሳት መሆን አለበት፡፡ እነሱም፡- ፍየል፣ በግ፣ ከብትና ግመል ናቸው፡፡ ከነዚህ ሌላ ያሉ እንሰሳት ወይም በራሪ አዕዋፋት ለእርድ አይቀርቡም፡፡ አንድ ፍየል ወይም በግ ለአንድ አባወራ ከነቤተሰቡ ይበቃዋል፡፡ በአንድ በሬ (ላም) ወይም ግመል ላይ ሰባት አባወራ ሊሳተፍ ይችላል፡፡
  2. የሚፈለግበት የዕድሜ ገደብ ላይ የደረሰ መሆን አለበት፡፡ የሚፈለገው የዕድሜ ገደብ፡- ለበግ ስድስት ወር፤ ለፍየል አንድ ዓመት፤ ለበሬ(ላም) ሁለት ዓመት፤ እና ለግመል አምስት ዓመት ነው፡፡
  3. እንሰሳው ግልጽ ከወጣ ነውርና ጉድለት የጸዳ መሆን አለበት፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አራት ዓየነት እንሰሳት ለእርድ ብቁ አይደሉም፡- ጠንጋራነቷ ግልጽ የሆነ እንሰሳ፤ ህመሟ ይፋ የሆነ እንሰሳ፤ አንካሳነቷ ግልጽ የሆነ እንሰሳ እና መረቅ የማይወጣት በጣም የከሳች እንሰሳ ›› (አል ነሳኢ 4371 አት ቲርሚዚ 1497)

የበዓል እርዱ ምን ይደርጋል?

  • ከእርድ ስጋ ላይ መሸጥ አይፈቀድም፡፡
  • እርድ የሚፈጽም ሰው፣ ስጋውን ሦስት ቦታ ከፍሎ፣ አንድ ሦስተኛውን ራሱንና ቤተሰቡን ይመግብበታል፤ ሌላኛውን አንድ ሦስተኛ (ለጓደኛና ቤተ ዘመድ) ስጦታ ያደርገዋል፤ የተቀረውን አንድ ሦስተኛ ደግሞ ለድሆች ይመጸውታል፡፡
  • አንድ ሰው፣ ለእርድ ሌላ ግለሰብን ቢወክል፣አለያም እርድ በመፈፀምና ስጋውን ለችግረኞች በማከፋፈል ሥራ ላይ ለተሰማሩ ታማኝ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የእርድ ገንዘቡን ሊሰጥ ይችላል፡፡