የተባረከው የጾም ፍቺ በዓል

የተባረከው የጾም ፍቺ በዓል

በዓላት፣ ከሃይማኖት መገለጫዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ መዲና በመጡበት ወቅት አንሣሮችን ከዓመቱ ቀናት በሁለት ቀኖች ውስጥ ሲፈነጥዙ፣ ሲጫወቱና ሲደሰቱ አግኝተዋቸው ነበር፡፡ እናም፡ ‹‹እነዚህ ሁለት ቀናት የምን ቀኖቻችሁ ናቸው?›› በማለት ጠየቋቸው፡፡ እነሱም፡ ‹‹ከኢስላም መምጣት በፊት- በጨለማው ዘመን እንደሰትባቸው የነበሩ ቀኖች ናቸው፡፡›› በማለት መለሱ፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ)፡- ‹‹አላህ እነዚህን ቀናት ከነርሱ በተሻሉ ሁለት ቀናት ተክቶላችኋል፡፡ የእርድ ዕለትና የፍስክ ዕለት›› አሏቸው፡፡ (አቡ ዳውድ 1134) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ በዓላት የሃማኖቶች መገለጫ እንደሆኑ ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹እያንዳንዱ ሕዝብ በዓል አለው፡፡ ይህ ደግሞ በዓላችን ነው፡፡›› (አል ቡኻሪ 909 /ሙስሊም 892)

በዓል በኢስላም

በኢስላም ውስጥ፣ በዓል አንድ የአምልኮ ዘርፍን ስላጠናቀቁ ደስታን የሚገልጹበትና አላህ(ሱ.ወ) ለዚህ አምልኮ ስለመራቸውና ስለገጠማቸው እሱን የሚያመሰግኑበት አጋጣሚ ነው፡፡ በዒድ ቀን፣ የሚያማምሩ ልብሶችን በመልበስ፣ ለከጃዮች መልካም በመዋል በሰዎች ልቦና ውስጥ ደስታን መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ኢስላም ያስተምራል፡፡ በማንኛውም የተፈቀዱ መንገዶች፣ የሁሉም ልቦና የደስታ ስሜት እንዲሰማውና የአላህን ጸጋ የሚያስታውስ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

 

የሙስሊሞች በዓል

በዓመት ውስጥ ሙስሊሞች የሚያከብሯቸው ሁለት በዓላት አሉ፡፡ ከሁለቱ ቀናት ውጪ ሰዎች እንደ በዓል አድርገው የሚያከብሯቸውን ቀናቶች ማክበር አይፈቀድም፡፡ እነኚህ በዓላት፡ የጾም ፍቺ በዓል ( የወርሃ ሸዋል የመጀመሪያ ቀን) እና የእርድ በዓል (የወርሃ ዙልሒጃ አስረኛ ቀን) ናቸው፡፡

የጾም ፍቺ በዓል

የጾም ፍቺ በዓል፣ የረመዳን የመጨረሻው ሌሊት ካለፈ በኋላ የሚከተለው የወርሃ ሸዋል የመጀመሪያው ቀን ነው፡፡ የጾም ፍቺ በዓል በመባል የሚጠራውም ለዚህ ነው፡፡ ይህ ቀን፣ ሰዎች ጾማቸውን በማጠናቀቃቸው፣ በጾማቸው አላህን ይገዙበት እንደነበረው፣ በመደሰት አላህን የሚያመሰግኑበት ዕለት ነው፡፡ ሙስሊሞች ይህን በዓል የሚያከብሩት፣ አላህ ጸጋውን ስላሟላላቸውና የረመዳንን ወር በሙሉ ለመጾም ስላደላቸው፣ አላህን እያመሰገኑ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ቁጥሮችንም ልትሞሉ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህን ደነገግንላችሁ)›› (አል በቀራ 185)

በኢስላማዊው ሕግ የተደነገጉና በዒዱ ዕለት የሚከናወኑ ነገሮች እንዴት ያሉት ናቸው?

  1. የበዓል ሠላት (የዒድ ሠላት)፡ ኢስላም፣ ሙስሊሞች ከሴቶችና ሕፃናት ጋር በመሆን በአንድነት ወጥተው ይህን ሠላት እንዲሰግዱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አስተምሯል፡፡ የመስገጃ ጊዜው፣ ፀሐይ ወጥታ የጦር ዘንግ ያክል ከፍ ካለችበት ቅጽበት ጀምሮ ከሰማይ መሐከል እስከምታዘነብልበት ጊዜ ይረዝማል፡፡

አፈፃፀሙ፡ የዒድ ሠላት ሁለት ረከዓ ነው፡፡ ኢማሙ ሲያሰግድ ቁርኣን የሚያነበው ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲሆን ከሠላቱ በኋላም ሁለት ኹጥባዎችን ያደርጋል፡፡ በዒድ ሠላት ‹‹አላሁ አክበር›› የሚለውን ቃል በእያንዳንዱ ረከዓ መጀመሪያ ላይ ደጋግሞ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በመጀመሪያው ረከዓ ላይ ፋቲሓን ማንበብ ሳይጀምር በፊት፣ ከመጀመሪያው የሠላት መግቢያ ተክቢራ ሌላ ስድስት ጊዜ ‹‹አላሁ አክበር›› ይላል፡፡ በሁለተኛው ረከዓ ላይ ደግሞ ከመጨረሻው ሱጁድ ሲነሳና ሲቆም ከሚለው ተክቢራ ሌላ አምስት ጊዜ ‹‹አላሁ አክበር›› ይላል፡፡

  1. የጾም ፍች ምጽዋት(ዘካተል ፊጥር)፡ አላህ (ሱ.ወ) በዒድ ዕለት፣ ቀንና ሌሊቱን ከሚበላው የሚተርፍ ነገር ያለው ሰው አገሬው ከሚመገበው ሩዝ ወይም ስንዴ ወይም ተምር አንድ ቁና ለሙስሊም ድሆችና ችግረኞች እንዲሰጥ ግዴታ አድርጓል፡፡ ይህም ድሆችና ችግረኞች በዒድ ዕለት ተቸግረው እንዳይውሉ ያደርጋቸዋል፡፡

የዘካተል ፊጥር መስጫ ጊዜ፡ የመጨረሻው የረመዳን ቀን ፀሐይ ከጠለቀችበት ሰዓት ጀምሮ፣ የዒድ ሠላት እስከሚሰገድበት ወቅት ድረስ ነው፡፡ ከዒዱ አንድ ወይም ሁለት ሌሊት ቀደም ብሎ መስጠትም ይቻላል፡፡

ዓይነትና መጠኑ፡ ከሀገሬው ምግብ የሆነ አንድ ቁና ሩዝ ወይም ተምርና የመሳሰሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ቁና የመስፈሪያ ልክ ነው፡፡ ነገር ግን በዘመናዊ የሚዛን ልኬት መሆኑ የተሻለ ነው፡፡ በግምት ሦስት ኪሎግራም ይሆናል፡፡

ለራሱ፣ ለሚስቱ ልጆቹ፣ እንዲሁም ቀለብ ለሚሰፍርላቸውና ለሚያስተዳድራቸው ሰዎች የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ላለ ፅንስ ማውጣትም ይወደዳል፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ካገሬው ምግብ አንድ ቁና ይወጣለታል፡፡

ሙስሊሞች ከዒድ ሠላት እየሰገዱ የሚያሳይ ምስል

ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን ሲደነግጉ፣ ምጽዋቱ፣ ጾመኛ በማላገጥና በመጫወት ምክንያት የሚያገኘውን ወንጀል እንዲያብስለተና ለችግረኞች ቀለብ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ከሠላት በፊት ላደረሳት፣ ተቀባይነት ያላት ምጽዋት ትሆናለች፡፡ ከሠላት በኋላ ላደረሳት ደግሞ እንደማንኛውም ሠደቃ፣ ሠደቃ ነች ብለን እንወስደዋለን፡፡ (አቡ ዳውድ 1607)

  1. በተፈቀዱ መንገዶች ሁሉ በመጠቀም፣ በተቻለ መጠን፣ በቤተሰብ ውስጥ፣ ትልቁንም፣ ትንሹንም፣ ወንዱንም፣ ሴቱንም፣ እንዲደሰትና እንዲዝናና ማድረግ በኢስላም የተደነገገ ተወዳጅ ተግባር ነው፡፡ የሚያምር ልብስ መልበስም እንዲሁ የተወደደ ነው፡፡ በዒድ ቀን መጾም ክልክል ነው፡፡ በዒድ ቀን የሚወደደው፣ በመብላትና በማፍጠር አላህን መገዛት ነው፡፡
  2. በኢድ ዋዜማ ሌሊቱን፣ እንዲሁም ወደ ዒድ ሠላት ሲወጣ፣ ‹‹አላሁ አክበር›› በማለት አላህን ማላቅ ኢስላም የደነገገው ተግባር ነው፡፡ የዒድ አልፊጥር ሠላት ተሰግዶ ሲያበቃ የተክቢራው ጊዜ ይጠናቀቃል፡፡ ይህ የሚደረገው፣ አላህ(ሱ.ወ) ወደ ጾም በመምራት፣ የተባረከውን የረመዳንን ወር ጾም ለማጠናቀቅ ስላበቃን፣ ለዋለልን ጸጋ እርሱን ለማመስገንና ደስታችንን ለመግለጽ ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ቁጥሮችንም ልትሞሉ፣ አላህንም ቅኑን መንገድ ስለመራችሁ ታከብሩትና ታመሰግኑት ዘንድ (ይህንን ደነገግንላችሁ)›› (አል በቀራ 185)

የተክቢራ አባባል፡ ‹‹አላሁ አክበር፤ አላሁ አክበር፤ ላኢላሃ ኢለላህ፤ አላሁ አክበር፤ አላሁ አክበር፤ ወሊላሂልሐምድ›› የሚል ነው፡፡

እንዲሁም፡ ‹‹አላሁ አክበሩ ከቢራ ወልሐምዱሊላሂ ከሲራ ወሱብሓነላሂ ቡክረተን ወአሲላ›› ይባላል፡፡

ወንዶች፣ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ፣ ሰዎችን በማይረብሽ ወይም በማያስቸግር መልኩ ተክቢራን መመላለሳቸው የተደነገገ ተግባር ነው፡፡ ሴቶች ግን ድምፃቸውን ዝቅ ማድረግ አለባቸው፡፡