የትክክለኛ ዳዕዋ(ጥሪ) መገለጫዎች (ወደ ኢስላም መጣራት)

አላህ(ሱ.ወ)፣ ትክክለኛ ጥሪ ከሌላ የጥሪ ዓይነት የሚለይበትን ባህሪ አብራርቷል፡፡ ትክክለኛ ጥሪ የሚከተሉት መገለጫዎች አሉት፡፡

  1. መረጃና ዕውቀት

አንድ ተጣሪ ወይም ዳዒ ወደርሱ በሚጠራበት ነገር ዕውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ የሚናገረውን ነገር ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆን አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ለነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላቸዋል፡- ‹‹በል፤ይህች መንገዴ ናት፤ ወደ አላህ እጠራለሁ፤ እኔም የተከተለኝም ሰው በግልጽ ማስረጃ ላይ ነን፡፡›› (ዩሱፍ 108)

አንተ ነብይ ሆይ! መንገዴ፣ መመሪያዬ ይህ ነው፤ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ወደ አላህ መጣራት ነው፤ ይህ ደግሞ እኔን የተከተሉ ተጣሪዎችም መንገድ ነው ብለህ ግለጽ እያላቸው ነው፡፡

አንድ ተጣሪ ወደ አላህ መንገድ ለማጣራት የግድ በርካታ ነገሮችን ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡ አንድን ሸሪዓዊ ሕግ ካወቀ ወደዚያ ነገር የመጣራት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ አላህን በብቸኝነት መገዛትን (ተውሒድን) ከተማረ፣ ይህንኑ ለሰዎች የማድረስ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ የኢስላምን መልካምነት ካወቀ ያወቀውን ያክል ለሰዎች ማስተላለፍ አለበት፡፡ የሚያውቀው አንዲትን የቁርኣን አንቀጽ ቢሆንም እንኳን ለሰዎች የማድረስ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንዲት አንቀጽ ብትሆንም ከኔ የሰማችሁትን አስተላልፉ፡›› (አል ቡኻሪ 3274) ሠሓቦችም እንዲሁ ነበሩ፡፡ ወደ ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ በመምጣት ኢስላምን ይቀበሉና በትንሽ ቀናት ውስጥ የሃይማኖቱን መሰረታዊ መርሆችንና መመሪያዎችን ይማራሉ፤ ከዚያም ወደ ጎሳዎቻቸው በመመለስ ወደ ኢስላም ጥሪ ያደርጋሉ፤ እንዲሰልሙ ያነሳሱዋቸዋል፡፡ ባህሪያቸው፣ ሰዎች ኢስላምን እንዲወዱና እንዲቀበሉ የሚጋብዝና የሚያበረታታ ነበር፡፡

  1. በዳዕዋ ውስጥ ብልሃትን መጠቀም

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹ወደ ጌታህ መንገድ በብልሃትና በመልካም ግሳጼ (በለዘብታ ቃል) ጥራ፤ በዚያችም እርሷ መልካም በኾነችው (ዘዴ) ተከራከራቸው፡፡›› (አል ነሕል 125)

ብልሃት ማለት፡ መስራት የሚገባን ነገር በሚጣጣም መልኩ መስራትና ከሚሰራው ስራ ጋር የሚስማማ የሆነን ጊዜና ቦታን መምረጥ ነው፡፡

የሰዎች ዝንባሌና ወደ ልባቸው የመግቢያ መንገድ የተለያየ ነው፡፡ ነገርን የመረዳትና የመገንዘብ ችሎታቸውም አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ስለሆነም ዳዕዋ አድራጊ ሰው ለእያንዳንዱ ሰው የሚስማማ የሆነን ዘዴ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ እጅግ በጣም ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ የሕይወት ገጠመኞችን ሊጠባበቅና ለዳዕዋ አመቺ በሆነ መልኩ ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡

የሰዎች ዝንባሌና ወደ ልባቸው የመግቢያ መንገድ የተለያየ ነው፡፡  ነገርን የመረዳትና የመገንዘብ ችሎታቸውም አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ስለሆነም ዳዕዋ አድራጊ ሰው ለእያንዳንዱ ሰው የሚስማማ የሆነን ዘዴ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ እጅግ በጣም ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ የሕይወት ገጠመኞችን ሊጠባበቅና ለዳዕዋ አመቺ በሆነ መልኩ ሊጠቀምባቸው ይገባል፡፡

ዳዕዋ ለሚያደርግላቸው ሰዎች ምንጊዜም ገርነትን፣ መልካም ግሳጼንና እዝነትን ማንጸባረቅ ይኖርበታል፡፡ እልህና ንትርክ ውስጥ የማይከት የሆነ ረጋ ያለ ውይይት ማካሄድም አስፈላጊ ነው፡፡  አላህ (ሱ.ወ) ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከሰዎች ጋር የነበራቸውን ገርነትና ይቅር ባይነት በአድናቆት ያወሳው ሲሆን፣ ልበ ደረቅ፣ ጨካኝ ቢሆኑ ኖሮ በዙሪያቸው የነበሩት ትተዋቸው ይበተኑ እንደነበረም አስጠንቅቋል፡፡ እንዲህም ይላል፡- 

‹‹ከአላህም በሆነ ችሮታ ለዘብክላቸው፤ዐመለ መጥፎ ልበ ደረቅም በሆንክ ኖሮ ከዙሪያህ በተበተኑ ነበር፡፡››  (አል ዒምራን 159)