የወለድ ቅጣት

የወለድ ቅጣት

  1. በወለድ የሚገለገል ሰው ከአላህና ከመልክተኛው ጋር ጦርነት በማወጅ እራሱን አጋፍጧል፡፡ በዚህም የአላህ እና የመልክተኛው ተዋጊ ጠላት ይሆናል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) አራጣን የሚበሉ ሰዎችን እንዲህ ይላል፡- ‹‹(የታዘዛችሁትን) ባትሰሩም ከአላህና ከመልክተኛው በኾነች ጦር (መወጋታችሁን) ዕወቁ፡፡ ብትጸጸቱም ለናንተ የገንዘቦቻችሁ ዋናዎች አሏችሁ አትበደሉም አትበድሉምም፡፡›› (አል በቀራ 279) ይህ ጦርነት መንፈሳዊና አካላዊ ጫናዎች አሉት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሰዎችን ያጋጠማቸው አለመረጋጋት፣ ጭንቀት፣ የሃሳብና የትካዜ ፈተና፣ በዚህ ጦርነት ምክንያት የመጣ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ የአላህን ትዕዛዝ በጣሰ ወይም ወለድ በበላ ወይም በወለድ ላይ በተባበረ ሰው ምክንያት የመጣ ጣጣ ነው፡፡ ይህ የዱንያ ወጤቱ ሲሆን ታዲያ የአኼራው የጦርነት ውጤትስ ምን ይሆን?
  2. በወለድ የሚገለገልና ወለድን የሚበላ፣ እንዲሁም በዚህ ላይ እገዛ የሚያደርግ ሰው ከአላህ እዝነት የተባረረና የተረገመ ነው፡፡ ጃቢር(ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፡- «የአላህ መልክተኛ ወለድ የሚበላን፣ ወኪሉን፣ ጸሐፊውን፣ ምስክሩንም ጭምር ረግመዋል፡፡» ‹‹ሁላቸውም እነሱ (በወንጀሉ) እኩል ናቸው፡፡›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ (ሙስሊም 1598)
  3. ወለድ የሚበላ ሰው የትንሳኤ ቀን የሚቀሰቀሰው እጅግ ዘግናኝና አስከፊ በሆነ ሁኔታ ነው፡፡ የአውድቅ በሽታ እንዳለበት፣ በጅን እንደተለከፈ ሰው እየተወላከፈና እየወደቀ ይነሳል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነዚያ አራጣን የሚበሉ ያ ሰይጣን ከመንካቱ የተነሳ የሚጥለው ሰው (ከአውድቁ) እንደሚነሳ ቢጤ እንጂ (ከመቃብራቸው) አይነሱም፡፡›› (አል በቀራ 275)
  4. የወለድ ገንዘብ ምን ቢበዛ ከበረከት የተሟጠጠ ነው፡፡ በወለድ እረፍትን፣ ስኬትንም፣ እርካታና እርጋታንም ማግኘት አይቻልም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አላህ አራጣን (በረከቱን) ያጠፋል ምጽዋቶችንም ያፋፋል፡፡›› (አል በቀራ 276)