የወላጆች መብት

የወላጆች መብት

ለወላጆች በጎ መዋል ከመልካም ስራዎች መካከል ከባዱና አላህ ዘንድ ብዙ ምንዳን ከሚያስገኙ ተግባሮች ሲሆን፣ አላህ (ሱ.ወ) እርሱን ከመገዛትና በአሃዳዊነቱ ከማመን ጋር አቆራኝቶታል፡፡

ለነርሱ በጎ መዋልና ጥሩ መሆን ጀነት ለመግባት የሚያስችል ወሳኝ ምክንያት አድርጎታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ወላጅ የጀነት የመሐለኛው በር ነው፤ ይህን በር ብትፈልግ ቸል በለው ወይንም ጠብቀው፡፡›› (አል ቲርሚዚ 1900)

  • በወላጆች ላይ የማመፅና ለነርሱ ክፉ የመሆን አደገኝነት

መለኮታዊ መመሪያዎች በሙሉ በአደገኝነቱና በከባድ ወንጀልነቱ የተስማሙበትና ከርሱም ያስጠነቀቁት ነገር ቢኖር ለወላጆች ክፉ መሆን ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለሠሓቦቻቸው፡ ‹‹አይከብዱ የከበዱ ወንጀሎችን አልነግራችሁምን?›› አሉ፡፡ ሠሐቦችም፡ «እንዴታ ይንገሩን እንጂ አንቱ የአላህ መልክተኛ» አሉ፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ)፡ ‹‹በአላህ ማጋራትና በወላጆች ላይ ማመፅ ናቸው፡፡›› አሉ፡፡ (አል ቡኻሪ 5918)

  • በአላህ ላይ ከማመፅ ውጭ ባለ ጉዳይ እነርሱን መታዘዝ

አላህ(ሰ.ወ) ላይ በማመፅ ወይም የአላህን ሕግ በመጣስ እስካላዘዙ ድረስ ወላጆች በሚያዙት ነገር ሁሉ ለነርሱ ፍጹም ታዛዥ መሆን ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም በፈጣሪ ላይ እያመፁ ለፍጡራን መታዘዝ አይፈቀድም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ሰውንም በወላጆቹ መልካም አድራጎትን አዘዝነው፤ ላንተም በርሱ ዕውቀት የሌለህን (ጣዖት) በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህ አትታዘዛቸው፡፡›› (አል አንከቡት 8)

  • ለነርሱ በጎ መዋል በተለይም ሲሸመግሉ

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፤ እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፤ በወላጆቻችሁም መልካምን ስሩ፤ በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው፤ አትገላምጣቸውም፤ ለነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው፡፡›› (አል ኢስራእ 23) አላህ (ሱ.ወ) የሰው ልጅ ለወላጆቹ በተለይም ከሸመገሉና ከደከሙ በኋላ ታዛዥ እንዲሆንና እንዳይገላምጣቸው ወይም እንዳይቆጣቸው አዟል፡፡ ኡፍ በማለት ቢሆንም ቃል ባይተነፍስም እንኳ በእነርሱ ላይ መበሳጨትና መቆጣት የለበትም፡፡

  • ከሃዲያን ወላጆች

አንድ ሙስሊም ወላጆቹ ከሃዲያን ቢሆኑም እንኳን ለነርሱ ፍፁም ታዛዥና በጎ የሚውልላቸው ሊሆን ይገባል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ለአንተ በርሱ እውቀት የሌለህን ነገር በኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፤ በቅርቢቱም ዓለም በመልካም ስራ ተወዳጃቸው›› (አል ሉቅማን 15) ለነርሱ በጎ ከመዋል ሁሉ እጅግ ታላቁና ጠቃሚው እነርሱን በጥሩ ስነምግባርና በጥበብ በተሞላ መልኩ ወደ ኢስላም መጥራት ነው፡፡