የውዴታ ጾም

የውዴታ ጾም

አላህ (ሱ.ወ) እንዲጾም ግዴታ ያደረገው በዓመት አንድ ወርን ብቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቻለና ፍላጎት ያለው፣ ከአላህ ተጨማሪ ምንዳን ለማግኘት የሚከጅል ሰው፣ ሌሎች ቀናትንም እንዲጾም ያበረታታል፡፡ ከነኚህ ቀናት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

  1. የዐሹራን ቀንና ከርሱ በፊት ወይም በኋላ ያለው ቀን፡፡ የዐሹራ ዕለት የሚባለው በኢሰላማዊው ቀመር መሰረት፣የወርሃ ሙሐረም አስረኛው ቀን ነው፡፡ ይህ ዕለት፣ አላህ(ሰ.ወ) ነብዩላህ ሙሳን(ዐ.ሰ) ከፈርዖን የገላገላቸውና፣ ፈርዖንን በባሕር ውስጥ ያሰጠመበት ዕለት ነው፡፡ ሙስሊሞች አላህ (ሱ.ወ) ነብዩላህ ሙሳን(ዐ.ሰ) ነፃ ስላወጣ፣ እርሱን ለማመስገንና የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ ለመከተል ሲሉ ይጾሙታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ ቀን ከፊቱ ወይም አንድ ቀን ከኋላው ጹሙ›› (አህመድ 2154) ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ስለዚህ ዕለት ጾም ተጠይቀው፣ ‹‹ያለፈውን ዓመት ወንጀል ያስምራል፡፡›› ብለዋል፡፡ (ሙስሊም 1162) 
  2. የዐረፋ ቀን፡ ዐረፋ፣ የወርሃ ዙልሒጃ ዘጠነኛው ቀን ነው፡፡ ዙልሒጃ፣ በኢስላማዊ ቀመር መሰረት አስራ ሁለተኛው ወር ነው፡፡ ይህ ቀን ሐጃጆች ዐረፋ በሚባል ቦታ ላይ በመሰብሰብ አላህን ሲለምኑና ሲማጸኑ የሚውሉበት ዕለት ነው፡፡ ከዓመቱ ቀናት ሁሉ የላቀና የበለጠ ቀን ነው፡፡ ሐጅ ላይ ላልተሳተፈ ሰው ይህን ቀን መጾም ይወደድለታል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስለ ዐረፋ ዕለት ጾም ተጠይቀው ሲመልሱ፡- ‹‹ያለፈውንና የመጪውን ዓመት ወንጀል ያስምራል፡፡›› ብለዋል (ሙስሊም 1162)
  3. ስድስቱ የሸዋል ቀኖች፡ ሸዋል አስረኛው ወር ነው፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ረመዳንን የጾመ፣ ከዚያም ከሸዋል ስድስት ቀናትን አስከትሎ የጾመ ሰው፣ አንድ ዓመት ሙሉውን እንደጾመ ይቆጠርለታል፡፡›› (ሙስሊም 1164)