ፍትሃዊነት – ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል

ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ ስነ ምግባራዊ አስተምህሮት መካከል፡

 ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በስነ ምግባራቸው ከሰዎች ሁሉ የላቁ ነበሩ

 

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)፣ እጅግ የላቀ ለሆነው የሰው ልጅ መልካም ስነ ምግባር ዓይነተኛ ተምሳሌት ነበሩ፡፡ ቁርኣን የሳቸውን ስነ ምግባር ታላቅ በማለት የገለጸው ለዚህ ነው፡፡ ባለቤታቸው እመት ዓኢሻም(ረ.ዐ) ስለርሳቸው ስነ ምግባር ሲናገሩ፡- ‹‹ስነ ምግባራቸው ቁርኣን ነበር፡፡›› ከማለት ሌላ የተሻለ የረቀቀ አገላላጽ አላገኙለትም፡፡ እርሳቸው፣ ለቁርኣን ስነ ምግባራዊ አስተምሮት ተግባራዊ ተምሳሌት ነበሩ፡፡

ፍትሃዊነት፡

  • ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የቅርብ ዘመዳቸው ላይም ቢሆን ፍትሃዊውን የአላህ ፍርድ ተፈፃሚ ከማድረግ ወደ ኋላ የሚሉ አልነበሩም፡፡ አላህም እንዲህ ሲል አዟል፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (በፍትሕ) ቋሚዎች፣ በነፍሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ፡፡›› (አል ኒሳእ 135)
  • የተወሰኑ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች፣ ጎሳዋ ውስጥ ክብር የነበራት፣ ሰርቃ የተያዘች አንዲት ሴት ላይ ኢስላማዊው ቅጣት ተፈፃሚ እንዳይሆንባት ለማማለድ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ በመጡ ጊዜ፣ ‹‹የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ፤ የሙሐመድ ልጅ ፋጢማ ብትስርቅ እንኳን እጇን እቆርጠዋለሁ፡፡›› ብለው መልሰዋቸዋል፡፡ (አል ቡኻሪ 4053 / ሙስሊም 1688)
  • በሰዎች ላይ ወለድ ወይም አራጣ እርም በተደረገ ጊዜ መጀመሪያ የጀመሩት ለርሳቸው እጅግ ቅርብ የሆነውን ሰው በመከልከል ነበር፡፡ ያም አጎታቸው ዐባስ(ረ.ዐ) ነው፡፡ በወቅቱ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹መጀመሪያ ውድቅ የማደርገው የኛን ወለድ ነው፤ የዐባስ ቢን ዐብዱልሙጠሊብን ወለድ (የወለድ ውል ሰርዣለሁ)፤ እነሆ ሁሉም የአራጣ ገንዘብ ውድቅ ሆኗል፡፡›› አሉ፡፡ (ሙስሊም 1218)
  • የአንድ ማኅበረሰብ ዕድገትና ስልጣኔ የሚለካው፣ ደካሞች ምንም ሳይፈሩና ሳያመነቱ ከጉልበተኞች መብታቸውን መውሰድ በመቻላቸው እንደሆነ አስተምረዋል፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በውስጧ ያሉ ደካሞች ያለ ምንም ፍርሃት መብታቸውን የማይወስዱበት ወይም የማያገኙበት ሕዝብ አይበለጽግም(አይድንም)፡፡›› (ኢብኑ ማጃህ 2426)