ፍቺ

ፍቺ

ኢስላም የጋብቻ ውል ዘላቂና ዘውታሪ መሆን እንዳለበት ይመክራል፡፡ ጋብቻው ሁለቱም ወገኖች ሞት እስኪለያያቸው ድረስ የሚቆይ መሆን አለበት፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ጋብቻን የጠበቀ ውል ሲል ጠርቶታል፡፡ በኢስላም፣ ጋብቻን ለተወሰነ የጊዜ ገደብ በሚል መፈፀም ጨርሶ አይፈቀድም፡፡

ኢስላም በጋብቻ ላይ ሰዎችን ሲያበረታታ ድንጋጌው የወጣው በምድር ላይ ለሚኖር ሰብዓዊ ፍጡራን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ የራሳቸው የሆነ ልዩ መገለጫ ባህሪያትና ስጋዊ ፍላጎቶች አሏቸው፡፡ በመሆኑም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና መንገዶች ሁሉ ሲዘጋጉ፣ የማስተካከያና የማሻሻያ ዘዴዎች ሁሉ ፍሬ አልባ ሲሆኑ፣ ከዚህ ውል እራሳቸውን እንዴት ነፃ ሊያደርጉ ወይም ሊያላቅቁ እንደሚችሉ ስርዓትን ደንግጎላቸዋል፡፡ በዚህም ለወንዱም ሆነ ለሴቷ ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚበጃቸውን መስመር ይዘረጋል፡፡ ብዙ ጊዜ በባልና ሚስት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ፍቺን ብቸኛ የችግራቸው መፍትሄ የሚያደርጉበት አጋጣሚ አለ፡፡ በቤተሰቡም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የሚያደርግበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም በባልና ሚስት መሐከል የተመሰረተው ትዳር የተፈለገበትን ግብ ሊመታ ባለመቻሉ አብረው ከመቆየታቸው ይልቅ ፍቺ የተሻለ ይሆናል፡፡

ከእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ለመውጣት ሲባል ፍቺ የተፈቀደው ለዚህ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ሌላ የትዳር አጋር መቀየር አለባቸው፡፡ ምናልባት ሁላቸውም ከመጀመሪያው የትዳር አጋራቸው ያጡትን ከዚህኛው ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ቢለያዩም አላህ ሁሉንም በችሮታው ያብቃቃቸዋል፡፡ አላህም ችሮታው ሰፊ ጥበበኛ ነው፡፡›› (አል ኒሳእ 130)

ፍቺ እራሱን የቻለ ስርዓት አለው፡

  • ፍቺ በወንዱ እጅ እንጂ በሴቷ እጅ አይደለም፡፡
  • አንዲት ሴት ከባሏ ጋር መኖር ካልቻለች፣ እሱ ደግሞ ሊፈታት ፍቃደኛ ካልሆነ፣ ዳኛ ዘንድ በመሄድ እራሷን ማስፈታት ትችላለች፡፡ ዳኛውም ያቀረበችው ምክንያት አሳማኝ ሆኖ ካገኘው ሊያፋታት ይገባል፡፡
  • አንዲት ሴት ከተፈታች በኋላ፣ ሁለት ጊዜ መመለስ ትችላለች፡፡ ነገር ግን ለሦስተኛ ጊዜ ከፈታት ሌላ ትክክለኛ ጋብቻ ፈፅማ እስካልተፈታች ድረስ ወደ መጀመሪያው ትዳሯ መመለስ አትችልም፡፡