ወለድ
በወለድ ውስጥ በደልና በሌላው ላይ ጉዳት ማድረስ የሚገኝበት በመሆኑ በኢስላማዊው ሕግ እርም የተደረገ ጭማሪ ገንዘብ ነው፡፡
የወለድ ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ ታዋቂዎቹና እርምነታቸው በጣም የጠበቀው፡ የብድርና የእዳ ወለድ ነው፡፡ ይህ በአንድ ገንዘብ ላይ ያለ ሸያጭ ወይም በሁለቱ ጠረፎች መካከል የእቃ ልውውጥ ሳይኖር የሚገኝ ጭማሪ ሲሆን ሁለት መልክ አለው፡፡
- የእዳ ወለድ
የብድሩ መክፈያ ወቅት ደርሶ ተበዳሪው በቃሉ መሰረት መክፈል ሳይችል ሲቀር በብድሩ መጠን ላይ የሚደረግ ጭማሪ ነው፡፡
ለምሳሌ፡ አቶ ሰዒድ ከአቶ ኻሊድ ከአንድ ወር በኋላ ለመክፈል 1000 ዶላር ተበደሩ እንበል፡፡ ወሩ ሲያልቅና የመክፈያው ወቅት ሲደርስ፣ አቶ ሰዒድ መክፈል ባይችሉና በቃላቸው መገኘት ቢያቅታቸው፣ አቶ ኻሊድ በተስማሙበት ወቅት ላይ ማለትም ወሩ እንዳለቀ የሚከፍሉት ከሆነ ያለምንም ጭማሪ ገንዘቡን ሊከፍሉት፣ ከተጨማሪ አንድ ወር በኋላ የሚከፍሉት ከሆነ ደግሞ 1100 ዶላር እንዲከፍሉት፣ ደግሞም መክፈል ካልቻሉ ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ 1200 ዶላር አድርገው ይከፍሉት ዘንድ እንደ ቅድመ ሁኔታ ቢያስቀምጡ፣ እነኚህ ጭማሪዎች የእዳ ወለድ ይባላሉ፡፡
- የብድር ወለድ
ይህ ደግሞ ከአንድ ግለሰብ ወይም ባንክ የሆነ ያክል ገንዘብ ሲበደር በስምምነታቸው መሰረት ብድሩን እስኪከፍል ድረስ በየዓመቱ ወይም ከዚያ በታች ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ወቅት በስምምነቱ መሰረት (ለምሳሌ 5 ፐርሰንት) እየተጨመረ ታስቦበት የሚከፍለው ጭማሬ ገንዘብ ነው፡፡
ለምሳሌ፡ አንድ ሰው የሆነን የመኖሪያ ቤት በመቶ ሺህ መግዛት ይፈልግና በቂ ገንዘብ አይኖረውም፡፡ ከዚያም ወደ ባንክ ያመራና ለቤቱ መግዢያ ከባንኩ አንድ መቶ ሺህ ይበደራል፡፡ ይኸውም ለአምስት ዓመታት በየወሩ እየተቆራረጠ የሚከፈል ሲሆን መጠኑም አንድ መቶ ሃምሳ ሺ ብር በሚል ስምምነት ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ ወለድ የብድር ወለድ ይባላል፡፡
ወለድ ከከባድ ወንጀሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አባዳሪ በማበደሩ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ከሆነም በዚሁ ስር የሚካተት ነው፡፡ ብድሩ የንግዱን ዘርፍ ለማጠናከር፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት፣ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት፣ ቤት ለመግዛት፣ ወይም የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችን ለመግዢያ የሚውል ቢሆንም ወለድ ካለው የተከለከለ ነው፡፡
ዕቃዎችን ዋጋቸውን ከተመናቸው በላይ በየጊዜው በካሽ በመክፈል መግዛት ግን ወለድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ መገልገያ መሣሪያን ወዲያው በሚከፈል አንድ ሺህ ዶላር መግዛት ወይም ይህንኑ መሣሪያ ለዕቃው ባለቤት፣ ለሻጩ በየወሩ መቶ ዶላር በመክፈል በአንድ ሺህ ሁለት መቶ ዶላር መግዛት ዓይነት ነው፡፡

