ወለድ በማህበረሰብና በግለሰቦች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት
ኢስላም በማህበረሰብና በግለሰብ ደረጃ በሚያስከትለው ጉዳትና ክስረት የተነሳ በወለድ ዙሪያ ጠበቅ ያለ አቋም ይዟል፡፡
- በሀብት መከፋፈል ተግባር ላይ በሀብታሞችና በድሆች መካካል ልዩነትን ይፈጥራል
ወለድ፣ ገንዘብ ከማህበረሰቡ ውስጥ በተወሰኑ ሰዎች እጅ ብቻ እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን በርካቶችን የገንዘብ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ በገንዘብ ክፍፍል ላይ ትልቅ ክፍተት የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ማህበረሰብ ድንበር ባለፈ መልኩ ሃብትን ያከበቱ የጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መፈንጪያ ይሆናል፡፡ የተቀሩት ስራ አጦች፣ ድሆችና ችግረኞች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ቂምን፣ ምቀኝነትንና ወንጀልን ከሚያስፋፉ ምክንያቶች ዋነኛው ነው፡፡
- ገንዘብን አለመቆጠብና የአባካኝነት ልማድ
ለአበዳሪ በሚገኝ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የብድር ስርዓት እንዲስፋፋ ነገሮችን ማግራራት፣ ብዙዎች ገንዘብን እንዳይቆጥቡና የአባካኝነት ልማድን እንዲያዳብሩ ያበረታታል፡፡ ምክንያቱም ተበዳሪ ባስፈለገው ጊዜ ገንዘብን በቀላሉ ያገኛል፡፡ በመሆኑም ስላለበትና ስለወደፊቱ አያስብም፡፡ የተበደረውን ገንዘብ በመዝናናትና በትርፍ ነገሮች ላይ ወሰን ባለፈ ሁኔታ ያባክናል፡፡ ብሎም፣ ከፍተኛ የሆነ የብድር ዕዳ ይከማችበትና ሕይወቱ ይጨናነቃል፡፡ ዕድሜ ልኩን በወሰደው ብድርና በተሸከመው እዳ እንደተሸማቀቀ ይኖራል፡፡
- ወለድ፣ ባለ ሃብቶች ሀገርን በሚጠቅም ነገር ላይ እንዳይሳተፉ የሚከለክል እንቅፋት ነው፡፡
በወለድ ስርዓት ውስጥ አንድ ባለ ሃብት በገንዘቡ ላይ ተጨማሪ የወለድ ገንዘብ የሚያገኝበት አጋጣሚ ይመቻችለታል፡፡ ይህ ደግሞ ለማህበረሰቡ ምን ያክል ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም፣ ገንዘቡን በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በንግዱ ዘርፎች እንዳያውል ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም፣ እነኚህ ስራዎች ልፋትና ድካምን የሚፈልጉና እንዲሁም የተወሰነ ያክል አደጋ ወይም ክስረት ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ በመስራት ፋንታ ገንዘቡን አበድሮ አራጣን መሰብሰብን ይመርጣል፡፡
- ወለድ የገንዘብ በረከት እንዲወገድ፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡
ማንኛውም በድርጅቶች ወይም በግለሰቦች ላይ የሚከሰት የኢኮኖሚ ውድቀትም ሆነ ከፍተኛ ኪሳራ መንስኤው በተከለከለው ወለድ ላይ መዘውተር ነው፡፡ ይህ ደግሞ አላህ (ሱ.ወ) የተናገረው የበረከት መወገድ አንዱ ውጤት ነው፡፡ ምጽዋትና ለሰዎች መልካም መዋል ግን ገንዘብ እንዲባረክና እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አላህ አራጣን (በረከቱን) ያጠፋል ምጽዋቶችንም ያፋፋል፡፡›› (አል በቀራ 276)
