ሁለት ባልና ሚስቶች አብረው ከሰለሙ፣ እንደ ወንድምና አጎት በኢስላም ሊጋቡ የማይፈቀድላቸው ካልሆኑ በስተቀር የጋብቻቸው ውል ባለበት ይጸናል፡፡ (ገጽ፣ 199 ተመልከት)

ሴቷ ሰልማ ባልየው ኢስላምን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ፣

በመስለሟ ብቻ የጋብቻው ውል ወደ ምርጫ ይቀየራል፤ ማለት ሚስት የመምረጥ መብት ይሰጣታል፡፡

  • የባሏን መስለም በትዕግስት መጠበቅ፡፡ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለባለቤቷ የኢስላምን እውነታ ማብራራትና መግለጽ አለባት፡፡ አላህ ወደ ቀጥተኛው መንገድ እንዲመራው መማጸን ይኖርባታል፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ ቢሆንም በዚህ ጥረቷ ከሰለመ መስለሙን እየተጠባበቀች እስከሆነ ድረስ በመጀመሪያው የጋብቻ ውል መሰረት በሚስትነቷ ከሱ ጋር መኖር ትጀምራለች፡፡ ከመስለሙ በፊት ግን ከእሷ ጋር እንዲተኛ ልትመቻችለት ወይም ልትፈቅድለት አይገባትም፡፡
  • ይሰልማል የሚል ተስፋ የማይጣልበት ነው በምትልበት ጊዜ ፍቺ የመጠየቅና የጋብቻውን ውል የማፍረስ መብት አላት፡፡

ከሰለመች ጊዜ አንስቶ በሁለቱም ሁኔታዎች ለካሃዲ ባሏ እራሷን ለግንኙነት ማመቻቸት አይፈቀድላትም፡፡ እራሷን ማመቻቸቷ እርም ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹አማኞችም መኾናቸውን ብታውቁ ወደ ከሃዲዎቹ አትመልሱዋቸው እነርሱ (ሴቶቹ) ለነርሱ የተፈቀዱ አይደሉም፤ እነርሱም (ወንዶቹ) ለነርሱ አይፈቀዱምና፡፡›› (አል ሙምተሒና 10)

በዚህ መመሪያ መሰረት አንዲት ሴት ከሰለመችበት ጊዜ አንስቶ የሚከተለውን መፈፀም ይኖርባታል፡

  1. ከሰለመችበት ጊዜ አንስቶ የምታገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅማ በብልሃትና በመልካም ተግሳጽ ባሏን ወደ ኢስላም መጥራት አለባት፡፡
  2. ባል ኢስላምን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ፣ እርሱን ለማሳመን ካልቻለች፣ ካልተሳካላት፣ ወይም በርካታ ሙከራዎችን አድርጋ ተስፋ የመቁረጥ ደረጃ ላይ ከደረሰች፤ በፍጥነት ከርሱ ጋር የምትፋታበትንና የምትለያይበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርባታል፡፡
  3. ለመፈታትና ከሱ ጋር ለመለያየት የሚወስድባት ጊዜ የሚረዝም ከሆነ በመካከላቸው ያለው የጋብቻ ውል ሕጋዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባል በዚህ መሐከል ከሰለመ የዒዳ ወቅት ቢጠናቀቅም በመጀመሪያው የጋብቻ ውል ትዳራቸው መቀጠል ይችላል፡፡ አስፈላጊው ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ ባል ካልሰለመና ዒዳው ካለቀ ግን የጋብቻው ውል ይፈርሳል፡፡
  4. የፍቺው ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ ሚስት ትዳር በመሰረተችበት ቤት ውስጥ መቆየት ትችላለች፤ ይሁን እንጂ ከሰለመችበት ጊዜ ጀምሮ ባለው ቆይታ ውስጥ ለግብረ ስጋ ግንኙነት እራሷን ለባሏ ማመቻቸት አይፈቀድላትም፤ እርም ነው፡፡