እባኮትን በመቀበል የስራችንን ማስቀጠል እና ማደግ ለማድረግ እርዳን። አላህ ይስጥዎት።
ምጽዋት የሚሰጠው ለነማን ነው?
ኢስላም ዘካ የሚሰጣቸውን ክፍሎች ገድቦ አስቀምጧል፡፡ አንድ ሙስሊም ከነኚህ ክፍሎች መካከል ለአንዱ ብቻ ወይም ከአንድ በላይ ለሆኑ አካሎች ዘካውን መስጠት ይችላል፡፡ ለሚገባቸው ክፍሎች ሊያከፋፍሉለት ለሚችሉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበሮች መስጠትም ይችላል፡፡ ዘካን በሀገር ውስጥ ማከፋፈሉ በላጭ ነው፡፡
ዘካ የሚገባቸው ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው፡
- ድሆችና ችግረኞች፡ አንገብጋቢና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላትና ለመሸፈን በቂ አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡
- ዘካን በመሰብሰብና በማከፋፈል ስራ ላይ የተሰማሩ የዘካ ሰራተኞች
- ከአሳዳሪው እራሱን በመግዛት ነፃ ለመውጣት ለሚጥር ባሪያ፡፡ ይህ ሰው ዘካን በመውሰድ ነፃነቱን ያውጃል፡፡
- ብድር ተበድሮ መክፈል ያቃተው ሰው፡ የተበደረው ብድር ለሰዎች በጎ ለመዋልና ለሕዝባዊ ጥቅም ወይም ለግል ጉዳይ ቢሆንም ልዩነት አይኖረውም፡፡
- በጦር ግንባር በአላህ መንገድ ላይ ለሚፋለም ጀግና፡ እነኚህ ደግሞ ከሃይማኖታቸውና ከአገራቸው ጠላትን በመመከትና በመጋፈጥ ላይ ያሉ ተዋጊዎች ሲሆኑ ማንኛውም ኢስላምን ለማስፋፋትና ለማሰራጨት፣ የአላህን ቃል ከፍ ለማድረግ የሚሰራ ስራም በዚሁ ስር የሚካተት ነው፡፡
- ልቦናቸው ከኢስላም ጋር በመላመድ ላይ ላሉ አዲስ ሙስሊሞች፡ እነኚህ፣ ከሃዲያን የነበሩ፣ በቅርቡ ኢስላምን የተቀበሉ፣ ወይም ይሰልማሉ ተብሎ የሚከጀሉና ተስፋ የሚጣልባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ለእነኚህ ዘካ የሚሰጧቸው ግለሰቦች ሳይሆኑ፣ መንግሳታዊ ክፍሎችና ጠቃሚነቱን ሊያገናዝቡና ሊመረምሩ የሚችሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ናቸው፡፡
- ስንቅ ያለቀበት መንገደኛ፡ ይህ ሰው በአገሩ ከፍተኛ ካፒታል ወይም ንብረት ያለው ቢሆንም ባለበት ሁኔታ፣ ስንቅ ካለቀበት፣ ከተቋረጠበትና ገንዘብ ካስፈለገው ዘካ ይሰጠዋል፡፡
አላህ (ሱ.ወ) ዘካ የሚገባቸውን ክፍሎች ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹የግዴታ ምጽዋቶች (የሚከፈሉት) ለድሆች፣ ለሚስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሰሩ ሰራተኞች፣ ልቦቻቸውም (በኢስላም) ለሚለማመዱት፣ ጫንቃዎችንም ነፃ በማውጣት፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሰሩ፣ በመንገደኞችም ብቻ ነው፡፡›› (አል ተውባ 60)

