በዒሳ(ዐ.ሰ) ዙሪያ ያለው የሙስሊም እምነት

  1. እርሱ ዒሳ(ዐ.ሰ) ከታላላቅ መልዕክተኞች አንዱና ስብዕናው እጅግ የላቀ ነው፡፡ እነኚህ ከመልዕክተኞች መካከል ስብዕናቸው እጅግ የላቀ ነቢያት የቆራጥነት ባለተቤት በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነርሱም ሙሐመድ’ ኢብራሒም’ ኑሕ’ ሙሳና ዒሳ ናቸው (አለይሂሙ ሰላም)፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በሚከተለው ቃሉ ዘክሯቸዋል፡- «ከነብዮችም የጠበቀ ቃልኪዳናቸውን በያዝን ጊዜ (አስታውስ)፤ ከአንተም፣ ከኑሕም፣ ከኢብራሂምም፣ ከሙሳም፣ ከመርየም ልጅ ዒሳም(በያዝን ጊዜ አስታውስ)» (አል አሕዛብ 7) ይላል፡፡
  2. ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) የኣደም ዝርያ ሰው ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ወደ ነገደ ኢስራኢል የላከው ሲሆን የተለያዩ ተዓምራት በርሱ እጅ እንዲፈፀሙ አድርጓል፡፡ ምንም ዓይነት የጌትነትም ሆነ የአምላክነት ደረጃ የለውም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለኢስራኢልም ልጆች ታምር ያደረግነው የሆነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ » (አል ዙኽሩፍ 59) ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ሕዝቦቹን፣ እሱንም ሆነ እናቱን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርገው እንዲይዟቸው ፈፅሞ አላዘዘም፡፡ ለነርሱ ያላቸው አላህ ያዘዘውን ብቻ ነበር፡፡ «ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ» (አል ማኢዳ 117)

    አንድ ሙስሊም ነብዩላህ ዒሳ(ዐ.ሰ) ከአላህ መልዕክተኞች መካከል ታላቅ መልዕክተኛ አንደሆኑ ያምናል፡፡ ነገር ግን አምላክ አይደለም፡፡ አልሞተም፤ አልተሰቀለምም፡፡

  3. እሱ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው፡፡ እናቱ መርየም፣ ፃድቅ፣ እውነተኛ፣ ለጌታዋ ፍፁም ታዛዥና ተገዢ፣ ጥብቅ፣ ጨዋና ድንግል ሴት ነች፡፡ ዒሳን(ዐ.ሰ) የፀነሰችው ያለአባት በአላህ (ሱ.ወ) ችሎታ ነው፡፡ የእርሱ አፈጣጠር ዘልዓለማዊ ተዓምር ነው፡፡ ልክ ኣደምን ያለአባት እና ያለእናት እንደፈጠረው ሁሉ እርሱንም ያለ አባት ፈጠረው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ ኣደም ብጤ ነው፡፡ ከዐፈር ፈጠረው ከዚያም ለርሱ (ሰው) ሁን አለው ሆነም፡፡» (አል ዒምራን 59)
  4. በርሱ በዒሳ(ዐ.ሰ) እና በነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) መሐከል የተላከ መልዕክተኛ የለም፡፡ ስለ ነብያችን ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ትንቢት ተናግሮ አብስሯል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «የመርየም ልጅ ዒሳም፡ የኢስራኢል ልጆች ሆይ! እኔ ከበፊቴ ያለውን ተውራትን የማረጋግጥና ከኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደ እናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ ባለ ጊዜ (አስታውስ) በግልጽ ታዕምራት በመጣቸውም ጊዜ ይህ ግልጽ ድግምት ነው አሉ፡፡» (አሥ ሠፍ 6)
  5. አላህ (ሱ.ወ) በእርሱ እጅ እንዲፈፀሙ ባደረጋቸው ታዓምራት እናምናለን፡፡ ለምፃምን ማዳኑን፣ አይነ ስዉራን ማብራቱን፣ ሙታንን ማስነሳቱን፣ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ስለሚበሉትና ስለሚያከማቹት መናገሩን እናምናለን፡፡ ሁሉም በአላህ ፍቃድ የተፈፀሙ ናቸው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ለነብይነቱና ለመልዕክተኝነቱ ትክክል ለመሆኑ ግልጽ የሆነ ማስረጃ አድርጎታል፡፡
  6. ዒሳ(ዐ.ሰ) የአላህ ባሪያና መልክተኛ ነው ብሎ እስከሚያምን ድረስ የአንድም ሰው ኢማን የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ አይሁዶች እርሱን ከገለጹበት የቅጥፈትና ፀያፍ ነገሮች ሁሉ የጸዳና የጠራ እንደሆነም እናምናለን፡፡ በዒሳ እውነተኛ ማንነት ዙሪያ የተሳሳቱትን የክርስቲያኖች አመለካከትም እናወግዛለን፡፡ ይኸውም እሱና እናቱን ከአላህ ሌላ አማልክት ማድረጋቸው ነው፡፡ ከፊላቸው እርሱ የአላህ ልጅ ነው ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ ከስላሴዎች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ አላህ እነርሱ ከሚሉት ሁሉ የላቀ ነው፡፡
  7. አላህ (ሱ.ወ) አይሁዶች ዒሳን(ዐ.ሰ) ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ ወደ ሰማይ ከፍ አደረገውና አሳረገው እንጂ እሱ አልተገደለም አልተሰቀለምም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የእርሱ ምስል በሌላ ሰው ላይ እንዲሆን አደረገ እናም ያንን ሰው ዒሳ መስሏቸው ገደሉት ሰቀሉትም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸውም (ረገምናቸው) አልገደሉትም አልሰቀሉትምም ግን ለነሱ (የተገደለው ሰው በዒሳ) ተመሰለ እነዚያም በርሱ ነገር የተለያዩት ከርሱ (መገደል) በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፡ ጥርጣሬን ከመከተል በስተቀር በርሱ ነገር ምንም ዕውቀት የላቸውም በእርግጥም አልገደሉትም፡፡ ይልቁንስ አላህ ወደርሱ አነሳው አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡ ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም በትንሳኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል፡፡ » (አል ኒሳእ 157-159) አላህ (ሱ.ወ) እርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ እንዲያርግ በማድረግ ጥበቃ አድርጎለታል፡፡ በመጨረሻው ዘመን ወደ ምድር ይወርዳል፡፡ በነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ሕግና ስርዓት ይዳኛል፡፡ ከዚያም በዚ‹ ምድር ይሞታል፤ በሷም ውስጥ ይቀበራል፡፡ ሌሎች ሰዎች እንደሚቀሰቀሱት የትንሳኤ ቀን ይቀሰቀሳል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- «ከርሷ (ከምድር) ፈጠርናችሁ በርሷም ውስጥ እንመልሳችኋለን ከርሷም በሌላ ጊዜ እናወጣችኋለን፡፡» (ጧሃ 55)