አላህ እንዳይጾሙ ፍቃድ የሰጣቸው ሰዎች

አላህ (ሱ.ወ) ከሰዎች መካከል ለተወሰኑ ሰዎች በረመዳን ወር አለመጾም እንዲችሉ ፍቃድ ሰጥቷል፡፡ ይህንንም ያደረገው ለነርሱ ከማዘን፣ ከማግራትና ከማቅለል አንፃር ነው፡፡ እኚህ ሰዎች የሚከተሉት ናቸው:-

1በመጾሙ የሚጎዳ ታማሚ፡- ለርሱ ማፍጠር ይፈቀድለታል፡፡ ከረመዳን በኋላ ሲሻለው ያፈጠረውን ይከፍላል፡፡ .

2 በሽምግልና ወይም ይድናል ተብሎ በማይከጀል በሽታ ምክንያት መጾም የማይችል ደካማ ማፍጠር ይፈቀድለታል፡፡ ለእያንዳንዱ ቀን አንድ ሚስኪን ያበላል፡፡ ይኸውም፣ በሀገሩ ከሚበላ የምግብ ዓይነት አንድ ኪሎ ተኩል በመስጠት ይሆናል፡፡

3 ተጓዥ መንገደኛ በጉዞው ላይ እያለ ከአራት ቀን ለማይበልጥ ጊዜ ሲያርፍ ማፍጠር ይችላል፡፡ ያንን ጾም የፈታበትን ቀን ከረመዳን በኋላ ሀገሩ ሲመለስ ይከፍላል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ብሏል፡- ‹‹በሺተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መጾም አለበት፡፡ አላህ በናንተ ገሩን (ይሻል) በናንተም ችግሩን አይሻም፡፡›› (አል በቀራ 185)

4 የወር አበባና የወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች፡፡ በነኚህ ሁለት ሁኔታዎች ላይ ያሉ ሴቶች መጾም በነሱ ላይ እርም ነው፡፡ መጾማቸው ትክክለኛ አይደለም፡፡ ከረመዳን በኋላ መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡ (ገጽ፣ 96 ተመልከት)

5 እርጉዝና አጥቢ፡፡ በራሳቸው፣ወይም በልጃቸው ላይ ጉዳትን ከሰጉ ወይም ከፈሩ፣ ማፍጠርና ቀኖቹን መክፈል ይችላሉ፡፡